ጥቅምት 15/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ "የውኃ ማማ ናት" መባሏ ሀገር የተትረፈረፈ የውኃ ሀብት አላት ማለት እንዳልሆነ ገለጸ።
ሚኒስቴሩ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ አላት ተብሎ የሚታሰበው የውኃ ሀብት መጠን 123 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ መሆኑን ጠቁሟል።

የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ሚካኤል መሐሪ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የውኃ ማማ መባሉ ከሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች አንጻር በከፍታ ቦታ ላይ ስለምትገኝ፣ ውኃን በነፃ ለጎረቤቶቿ እንደምትሰጥ ለመግለጽ ነው ብለዋል።
አክለውም፣ እንደ "ወርልድ ሪቪው" መረጃ፣ ሀገራት በዓመት በአማካይ 1 ሺሕ ሜትር ኪዩብ እና ከዛ በታች የሆነ የነፍስ ወከፍ ውኃ ድርሻ ካላቸው የውኃ ሀብት እጥረት ውስጥ ናቸው።
ኢትዮጵያም ከዚህ ስጋት የምታመልጥ አይደለችም በማለት፤ የሀገሪቱ የውኃ ሀብት ውስንነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከግብጽ በኩል በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት 'የጎርፍ አደጋ ደርሶብኛል' በሚል ከሰሞኑ በቀረበው ክስ ዙሪያ ጥያቄ የቀረበላቸው አማካሪው፤ ኮርፖሬሽኑ የግድቡን ጉዳይ በየቀኑ እንደሚከታተል ገልጸዋል።
"የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጉዳይ በየቀኑ የምንከታተለው ነው። አካባቢው ላይ የቴሌ ስቴሽኖችን በመትከል በየቀኑ ምን ያህል ውኃ ይገባል፣ ምን ያህል ውኃ ከግድቡ ይወጣል የሚለው ስለሚታይ የተነሳው ክስ ሐሰት ነው።" ብለዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም የወንዞችን የጥልቀት መጠን፣ የከርሰ ምድር ውኃን መጠንና ጥልቀት እንዲሁም ከውኃ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በወረቀት ሲሰበስብ እንደነበር ተገልጿል።
በአሁኑ ጊዜ ግን የተፋሰስ ሀብት መረጃ ክትትል ስርዓት (Basin Monitoring Strategy)ን በማዘጋጀት በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑ ተመላክቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ