መስከረም 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በኃላ የተሽከርካሪ ሰሌዳን መቀየሯን የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር አስታውቋል

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ታርጋ ላይ 17 ዓይነት ቀለማት ስንጠቀም የነበረ ሲሆን፤ አዲሱ ሰሌዳ ላይ ሦስት ቀለማት ብቻ እንዲኖር መደረጉን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በተጨማሪም ሰሌዳው ላይ መለያ የነበረው የክልል ስያሜ ዓለም አቀፍ ሕግን በተመለከተ ወደ ኢቲ ወይም ETH መቀሩንም ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ አስታውቋል።

በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያ አዲሱን የተሸከርካሪ ሰሌዳ መቀየሯን በማስመልከት ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ በ1994 ዓ.ም ለመጨረሻ ግዜ የሰሌዳ ቁጥር ለውጥ ከተደረገ ወዲህ ያሁኑ ከ23 ዓመት በኃላ የመጀመሪያው ቅየሪ መሆኑ ተገልጿል።

በግምት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪ እንደ ሀገር በመኖሩ አዲስ የሰሌዳ ቁጥር ለማዘጋጀት እንደታሰበም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የተሽከርካሪ ሰሌዳ (ታርጋ) ለውጥ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ መፅደቁ ይታወሳል።

መመሪያው የተሸከርካሪ የመለያ ቁጥር ሰሌዳ ዓይነቶችና ምልክቶች መወሰኛ እና የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 1050/2017 የተሰኘ ነው።

መግለጫውን የሰጡት የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የሰሌዳ ለውጡ ዋና ምክንያት ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ታሳቢ ያደረገ ሰሌዳ እንዲኖር ለማድረግ ነው።

Post image

እንዲሁም ከዚህ ቀደም በነበረው የተሽከርካሪ መለያ ቁጥር ሰሌዳ የአመራረት እና አሰረጫጨት ችግር፣ የአወጋገድ ችግር፣ የአሰራር ክፍተት፣ የሀብት ብክነት፣በሲስተም የተደገፈ ሥራ አለመኖር ችግር እንደነበር ተገልጿል።

አዲሱ የታርጋ የተገልጋዩን ፍላጎት የሚያሟላ የተጠቃሚውን ፍላጎት የሚያሟላ ስለመሆኑም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

አዲሱን የሰሌዳ ቁጥር ላይ አዲስ የተቀመጠዉ አንድኛው ልዩ የሆነ የፌደራል ስቲከር መዘጋጁቱ መሆኑም ተገልጿል።

ሌላው ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለ በሀገሪቱ የሚመዘገቡ ሁሉም ተሸከርካሪዎች የሚለጥፉት የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ላይ፤ የኢትዮጵያ ካርታ እንዲሁም ኢትዮጵያ ባጸደቀችው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት የተሰጣትን ሀገራዊ ልዩ ምልክት " ETH " እና " ኢት " የሚል የግእዝ ፊደላት እና የላቲን ፊደላት ይዘት እንዲኖረው ይደረጋል ተብሏል።

የተለየ የሕግ ባለሙያዎች የሚያነቡት የተለየ ፅሁፍ የተዘጋጀለት መሆኑንም አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።

ከዚህ ቀደም አንድ አሽከርካሪ ከየት እንደመጣ በግልፅ ስለሚገልፅ የተለያዩ ችግሮች ሲደርሱበት ቆይቷል ያሉ ሲሆን፤ ይህን የሚቀርፍ ነው ብለዋል።

አዲሱ ታርጋ ኮፒ ማድረግ ወይም ተመሳሳዩን መስራት አያስችልም ሲሉም በማስታወቂያው ወቅት ገልጸዋል።

በተጨማሪም መግለጫዉ የሰጡት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድኤታ በርሆ ሀሰን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም ታርጋ ላይ 17 ስንጠቀም የነበረ ሲሆን አዲሱ ላይ ወደ ሶስት ቀለማት ብቻ እንደሚኖር ገልጸዋል።

Post image

በአጭር ጊዜ ውስጥም ይህንን ሰሌዳ ወደ ሥራ ይገባል የተባለ ሲሆን፤ 50 ሺሕ ታርጋ ወደ ሀገር መግባቱም ተነስቷል።

ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር ለዚህ የታርጋ ለዉጥ ምን ያህል ወጪ እንደወጣበት የተጠየቀ ቢሆንም ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ከመናገር ተቆጥበዋል።

በተጨማሪም የታርጋ ለውጡን አስመልክቶ ወጪውን የተሽከርካሪዉ ባለቤት እራሱ እንደሚሸፍንም በመግለጫው ተነስቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ