መስከረም 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) አባልነት ድርድር ሂደት 6ኛው የሥራ ቡድን ስብሰባ ላይ፤ በሁለትዮሽ ንግድ ድርድር ዙሪያ 18 ሀገራት ጋር ድርድር ማድረግ መጀመሯን ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት 6ኛ የሥራ ቡድን ስብሰባ ባለፈው ሳምንት በስዊዘርላንድ ጄኔቫ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፤ ይህም ስብሰባ ኢትዮጵያ የድርጅቱን አባልነት ጥያቄ ባቀረበች ከ20 ዓመታት በላይ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ የተመዘገበበት እንደነበር ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የድርድሩ ቡድን መሪ፣ ዋና ተደራዳሪ እና የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የድርድር ሂደቱን አስመልክቶ፤ በትናንትናው ዕለት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን እና ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያለው የንግድ ትስስር እንድታጎለብት ለማድረግ ብርቱ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ በፊት የሁለትዮሽ ንግድ ድርድር ለማድረግ ከማንም ሀገር ጋር ስምምነት አለመደረጉን የገለጹት ሚንስትሩ፤ በቅርብ በተካሄደው ስብሰባ ግን ከ18 ሀገራት ጋር ድርድር እንደሚደረግና ከእነዚህም መካከል 6ቱ በስብሰባው ላይ ስምምነት እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ቀሪዎቹ ሀገራት እስከ ሕዳር 30 ባለው ስምምነት እንደሚያደርጉ አያይዘው ገልጸዋል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት አካል መሆን ማለት፤ ተገማች፣ የሚተበነበይ፣ በሕግና ስርዓት የሚመራ የባለ ብዙ ወገን የገበያ ስርዓት ውስጥ መቀላቀል እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን በተደረገው ስብሰባ ላይ የተገኘው ልዑክ ቡድን ከአባል ሀገራት ከ200 በላይ ጥያቄዎች እንደቀረበለት በመግለጽም፤ ለአባልነት ጥያቄው ዓለም ባንክን ጨምሮ 31 ሀገራት ድጋፍ መስጠታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ድርጅቱ ከተመሠረተበት 1995 ዓ.ም ጀምሮ የአባልነት ጥያቄ ማቅረቧን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ በድርድር ሂደቱ በተለይም ከ5ኛው የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባ ወዲህ በጣም ፈጣን ውጤት የተመዘገበበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮው 6ኛው የሥራ ቡድን ስብሰባ ላይ በተደረገው የድርድር ሂደት፤ ኢትዮጵያ የብዙ ወገን ድርድር እና የሁለትዮሽ ድርድሮችን በማካሄድ ውሳኔዎችን ማሳለፍ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም መሰል የገበያ ዕድል ድርድሮች እንደሚካሄዱ አስታውቀዋል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት 30 አባል ሀገራት በመያዝ እ.ኤ.አ ጥር 1 ቀን 1995 የተመሠረተ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ 166 አባል ሀገራትን በአባልነት ይዟል።

ድርጅቱ ዓለም አቀፍ የንግድ ደንቦችን በማውጣት የዓለምን 98 በመቶ ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የንግድ ሥርዓትን መፍጠር ችሏል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ