መስከረም 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) "ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት" የተሰኘውና 5 የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የመሠረቱት ቅንጅት፣ በቅርቡ በጉራጌ ዞን የተነሳውን ግጭት ጨምሮ በሀገሪቱ ውስጥ እየተባባሱ ባሉ የጸጥታ እና የፖለቲካ ውጥረቶች ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል።
ቅንጅቱ በጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ በመስቃን ወረዳ በሁለት ወንድማማች ሕዝቦች መካከል የተፈጠረውን ግጭት የጸጥታ ኃይሉ ለማረጋጋት ያደረገውን ጥረት በበጎ እንደሚመለከት የገለጸ ሲሆን፤ ችግሩ በስክነትና በወንድማማችነት መንፈስ እንዲፈታ ጥሪ አቅርቧል።
ቅንጅቱ በመግለጫው፤ ሕዝቡ በአዲስ ዓመት ተስፋ እንዲሰንቅ ከዚህ ቀደም የነበረው አካሄድ ግጭቶችን ማቆም እና የፖለቲካ እሥረኞችን መፍታት እንደነበር አስታውሷል።
ሆኖም በተያዘው አዲስ ዓመት እገታ፣ ግድያ፣ ዛቻ፣ የፖለቲካ ውጥረቶች እና የኑሮ ጫና ካለፈው ዓመት የቀጠሉ ሥርዓት-ወለድ ችግሮች መሆናቸውን በመግለጽ፤ የችግሮቹ መጠንና ቦታ ብቻ ተቀያይሮ ሕዝቡ አሁንም በችግር ውስጥ እንዲኖር አድርጓል ብሏል።
ለዚህም ለአብነት፣ በመስከረም 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ቡታጅራ በስናኖ ሴራ የተባለው የአካባቢው ባህላዊ እሴት አከባበርና ባለቤትነት ዙሪያ በተነሳው ብጥብጥ ጉዳቶች መከሰታቸውን አንስቷል።
በተጨማሪም፣ በሰሜን ወሎ ዞን ከወልዲያ 20 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው ሣንቃ ከተማ በመስቀል በዓል ዕለት የተፈጸመ ጥቃት የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ በመግለጫው ተነስቷል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ በላሊበላ ከተማ ከሚገኙ ቅርሶች መካከል በሆነው ገነተ-ማርያም ቤተክርስቲያን አቅራቢያ በደረሰ ጥቃት ጉዳት የደረሰበት ሰው ባይኖርም፤ አካባቢው ነዋሪዎች "የቅርሱን መሠረት ነክቶት ይሆን ወይ? ብለን ሥጋት ገብቶናል" ማለታቸውን ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ገልጿል።
በመጨረሻም ጥምረቱ በሀገሪቱ ያሉ ጦርነቶች በተኩስ አቁምና በድርድር እንዲቋጩ፣ ሕዝቡ የሰላም አየር እንዲተነፍስ እንዲሁም፤ ወንድም ወንድሙን የሚገድልበት ሁነት በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስቧል።
በዚህም ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ሕዝብን በማስቀደም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
"ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት" አዲስ ዓመትን ተከትሎ በጉራጌ ዞንና በሰሜን ወሎ ያጋጠሙ ግጭቶች ላይ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጠየቀ
