መስከረም 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ እና የፓኪስታን እስላማዊ ሪፐብሊክ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር እና በመከላከያና አቪዬሽን ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል።

ይህ ስምምነት የተደረሰው በፓኪስታን የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጀማል በከር አብዱላ (ዶ/ር) እና የፓኪስታን የፌዴራል መከላከያ ሚኒስትር ካዋጃ ሙሐመድ አስፍ በዛሬው ዕለት ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት ላይ ነው፡፡

Post image

በዚህም በኢትዮጵያና በፓኪስታን መካከል ያለውን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብር፤ ሰላምና ደህንነት፣ መከላከያ፣ አቪዬሽን፣ አየር ንብረት ለውጥ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ ባህልና ቱሪዝምን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተወያይተዋል።

አምባሳደር ጀማል በፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መርህ ላይ ተገንብቶ በማንም ሀገር ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳያደርስ፤ ክልላዊ ውህደትን በማጎልበት በቅርቡ ስለተመረቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለፌዴራል ሚኒስትሩ ገለጻ አድርገዋል።

በመቀጠልም አምባሳደሩ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ እያስመዘገበች ያለችውን ጉልህ እድገት አጽንኦት ሰጥተው የገለጹ ሲሆን፤ አሁን ካለው የካራቺ በረራ በተጨማሪ ወደ ፓኪስታን የበረራ መዳረሻዎችን ለማስፋት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

Post image

የፓኪስታን የፌዴራል መከላከያ ሚኒስትር ካዋጃ ሙሐመድ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን እና የሀገሪቱን ብልፅግና ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እየተገበሯቸው ያሉ ሥራዎችን አድንቀዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን፣ ደህንነትን እና መረጋጋትን በማስፈን ረገድ ኢትዮጵያ የምትጫወተውን ቁልፍ ሚና በማድነቅም፤ ፓኪስታን ለእነዚህ ጥረቶች ያላትን ድጋፍ እንደምትሰጥ መረጋገጣቸውን አሐዱ በፓኪስታን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ