መስከረም 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 በጀት ዓመት በቱሪዝም ዘርፍ ላይ በተሰሩ ሥራዎች ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በኢትዮጵያ እንዲካሄዱ መደረጉ የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ አስታውቀዋል፡፡
በዛሬው ዕለት በተካሄደው 6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ፤ የኢኮኖሚ መዛባቶችን የሚያርሙ ፈጣን እና መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻዮች ተግባራዊ መደረጋቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በዚህም የመንግሥት ገቢን፣ የወጪ ንግድ እና የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ለማሳደግ መቻሉ ጠቁመዋል፡፡
የልማት አቅጣጫ ትኩረት ውስን ከሆኑ ዘርፎች ወደ ባለብዙ ዘርፍ የኢኮኖሚ መሠረቶች በመቀየር ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ በዚህ ረገድ ኢኮኖሚውን ከጥገኝት በማላቀቅ ወደ ኢኮኖሚያዊ ሉኣላዊነት ለማሸጋገር የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ እንደተከፈተ ተናግረዋል፡፡
የኢኮኖሚ ለውጥ መሠረቶች ያሉትን አቅሞች በማወቅ፣ በችግር ውስጥ እድልን በማየት፣ በፈጠራ፣ በፍጥት እና ዘላቂ ግቦችን በማሳካት ላይ ያተኮሩ ስራዎች መሰራታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበሩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በማልማት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲስፋፉ ይደረጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የማህበረሰቡን ጥቅም የሚያስጠብቁ የማህበረሰብ ቱሪዝም ፕሮጀክቶችን በመተግበር የነዋሪውን ወግ እና ታሪክ የሚሳዩ የባህል ማዕከል አጣምሮ በመገንባት ለጎብኚዎች እና ለነዋሪዎች ጭምር ምቹ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ አጠቃላይ ሀገራዊ እድገት ማፋጠን ማስቻሉ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ በበጀት ዓመቱ የቱሪዝም ዘርፍን ማሳደግ መቻሉ ጠቁመዋል፡፡
በቱሪዝም ዘርፍ ላይ በኢትያጵያ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች ማካሄድ መቻሉን፤ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በማብራሪያቸው አስረድተዋል፡፡
የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት እና የመሠረተ ልማት በማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አክለውም በቱሪዝም አገልግሎት ሀገራዊ ሀብት መፍጠር እንደሚቻል በማመን፤ በመንግሥት የተጀመሩ ሥራዎች በማጠናከር ቀጣይነት ያላቸው ናቸው ብለዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኢትዮጵያ በ2017 ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች መካሄዳቸው ተገለጸ
የማሕበረሰብ ቱሪዝም ፕሮጀክትን በመተግበር ለጎብኚዎች እንደሚቀርብ ተነግሯል
