መስከረም 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ሩሲያ እና ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለማቋቋም የኒውክሌር ትብብር ስምምነት የድርጊት መርሃ ግብር፤ በሮሳቶም እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን መካከል ተፈራረመዋል።
ይህ ሰነድ በኢትዮጵያ የኑክሌር መሠረተ ልማት ለመገንባት፣ ለኑክሌር ዘርፉ ሠራተኞችን ለማሰልጠን፣ ለኑክሌር ኃይል የቁጥጥር ማዕቀፎችን ለማጠናከር፣ የኑክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል ለማቋቋም እንዲሁም የኑክሌር ሳይንስን ለሰላማዊ አጠቃቀሞች ትብብር ለማስፋፋት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
ሰነዱ ሁለቱ ሀገራት የፕሮጀክቱን ቴክኒካል እና ኢኮኖሚያዊ መሰረት በማድረግ፤ ዝርዝር የግንባታ እቅድ እና "ፍኖተ ካርታ" በማዘጋጀት፤ ወደ ተግባር ለመግባት የመንግሥታት ስምምነት ለማድረግ የሚያስችል ስለመሆኑም ተመላክቷል።
በዚህም መሠረት የሩሲያ መንግሥት የኒውክሌር ኮርፖሬሽን ሮሳቶም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሌክሲ ሊካቼቭ እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ ቭላድሚር ፑቲን እና ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የተፈረመውን ሰነድ ተለዋውጠዋል።
የፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መካከል የተደረገው ውይይት አካል መሆኑ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሩሲያ የኑክሌር ኢንዱስትሪን 80ኛ ዓመት በዓልን ለመዘከር በሞስኮ ከተካሄደውን ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ፎረም ጎን ለጎን፤ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በዚህም ውይይት፤ የኃይል ማመንጫ፣ ግብርና፣ የጤና ጥበቃ ልማት እና የመከላከያ ትብብርን ጨምሮ ሰፊ ጉዳዮች ላይ መነሳታቸው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፑቲን ቀጣዩን ስብሰባ በኢትዮጵያ ዋና ከተማ እንዲያካሂዱ በመጋበዝ፣ ወደ ሩሲያ ያደረጉት ጉብኝት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን በበኩላቸው፤ በሩሲያ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት በዘላቂ ሁኔታ እያደገ መሆኑን ገልጸው፤ "ንግድም እየጨመረ ነው" ብለዋል።

ውይይቱ ለማኅበረሰብ አገልግሎት የሚውል ንፁህ ኃይል ምንጭ የሚውል የጋራ የኒኩሊየር ኃይል ማመንጫ የማልማት ስምምነቶችን ጨምሮ የጋራ ፍላጎት በሆኑ ጉዳዮች ላይ መካሄዱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።
ቀደም ሲል የኒጀር የማዕድን ሚኒስትር ኦስማን አባርቺ ከሮሳቶም ጋር በመተባበር ሀገራቸው ሁለት 2 ሺሕ ሜጋ ዋት የኒውክሌር ማመንጫዎችን ለመገንባት ስምምነት መፈጸማቸው ይታወሳል።
ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ብቸኛዋ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ያላት ሀገር ስትሆን፤ ግብፅ ደግሞ ሪአክተሮች በመገንባት ላይ መሆኗ ይታወቃል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ