መስከረም 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ እንደ ሽንኩርት እና ቲማቲም ያሉ የግብርና ምርቶች ዋጋ በእጥፍ በመጨመሩ ከፍተኛ የኑሮ ጫና ፈጥሮብናል ሲሉ ሸማቾች ቅሬታቸውን ለአሐዱ አቅርበዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንዳሉት፤ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ የቲማቲም ዋጋ ከ40 ወደ 90 ብር፣ የሽንኩርት ዋጋ ከ90 ወደ 150 ብር ከፍ ብሏል።
"የዋጋ ንረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ ከፍተኛ የኑሮ ጫና ፈጥሮብናል" የሚሉት ቅሬታ አቅራቢ የከተማዋ ነዋሪዎች፤ የሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም የዋጋ ማረጋጋት ሥራ እንዲሰራ ጠይቀዋል።
አሐዱ ለቅሬታው ምላሽ ለማግኘት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮን ጠይቋል።
የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ብርሃኑ በሰጡት ምላሽ፤ ተቋማቸው በገበያ ማዕከላት እና በሰንበት ገበያዎች ላይ የዋጋ ቁጥጥር እንደሚደረግ አስታውሰው፤ በግል ሱቆች ውስጥ የሚሸጡ የሸቀጣሸቀጥ ምርቶችን የዋጋ ተመን መቆጣጠር እንደማይቻል ገልጸዋል።
አቶ አሸናፊ አክለውም፣ ቢሮው የሸቀጣሸቀጥ ዋጋን ለማረጋጋት በአቅርቦት ላይ በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ላይ አንድ ኪሎ ግራም የሽንኩርት ዋጋ በ90 ብር እየተሸጠ ነው።
ማህበረሰቡም የዋጋውን ሁኔታ ለማረጋጋት በሚደረገው ጥረት ተባባሪ እንዲሆን፤ በተለይ በሰንበት ገበያዎች ላይ እየቀረበ ያለውን ምርት እንዲጠቀምም የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች የዋጋ ንረት ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሮብናል ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ዋጋ ለማረጋጋት አቅርቦትን መጨመር ላይ እየሰራ መሆኑን ገልጾ፤ ነዋሪዎች ከሰንበት ገበያዎች እንዲሸምቱ መክሯል
