መስከረም 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር፣ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን፣ ከኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት እና ከአዲስ አበባ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በግንባታ ላይ የሚፈጠሩ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ትናንት መስከረም 15 ቀን 2018 ተፈራርሟል።

ተቋማቱ በግንባታ ደህንነት እና ጤና ላይ ያተኮረ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፤ በውይይቱ ላይም በግንባታ ወቅት ለአደጋ ስለሚያጋልጡ ነገሮች እና መደረግ ስለሚገባቸው የመፍትሄ ሥራዎች በስፋት ተነስቷል።

በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ (ዶ/ር) ከትራፊክ አደጋ በመቀጠል በግንባታ ሳይት ላይ የሚደርስ አደጋ እየጨመረና እየከፋ መምጣቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም የሚደርሱ አደጋዎችን ለማስቀረት እንዲያስችል በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በሙሉ በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

የተደረገው የመግባቢያ ስምምነትም ይህንን ችግር ለመፍታት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ታምራት ሙሉ (ኢ/ር) በበኩላቸው፤ ዘርፉ በርካታ ሀብት የሚንቀሳቀስበት መሆኑን ገልጸው "በአግባቡ መመራት ከተቻለ ሀገርን መቀየር የሚችል ትልቅ አቅም አለው" ብለዋል።

ነገር ግን በአግባቡ መቆጣጠር ካልተቻለም በዛው ልክ ሊመለስ የማይችለውን የሰው ልጅ ነፍስ የሚቀጥፍ መሆኑን አንስተዋል።

በዘርፉ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እጥረት እንደሌለም ያነሱም ሲሆን፤ ችግሩ የአተገባበር እና የግንዛቤ እጥረት በመሆኑ ተፈፃሚ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪው ፈጣን ለውጥን እያሳየ የሚገኝ ቢሆንም ከዚህ በተለየ መልኩ ደግሞ በሠራተኞች የሥራ ላይ ደህንነት ለውጥ እየታየበት አይደለም ሲሉ የገለጹት ደግሞ፤ የአዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ም/ ዋና ዳይሬክተር አበበ እሸቱ (ኢ/ር) ናቸው።

Post image

የአዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ህይወት ሳሙኤል (ኢ/ር) ደግሞ፤ በተለይም በአዲስአበባ በርካታ የግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በዘርፉ በየጊዜው በርካታ የሰው ሕይወት የሚጠፋበት በመሆኑም በግንባታ ሥራ ላይ የሚደርስ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል ሥራ በሰፊው እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የዚሁ ሥራ አካል የሆነው የተደረገው ውይይትና ስምምነትም የግንባታው ዘርፍ እንዲያድግና አደጋዎች እንዲቀንሱ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸው፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚሰራበት ተናግረዋል።

በግንባታ ሳይት ላይ በተደጋጋሚ ከሚታዩ የአደጋ መንስኤዎች ውስጥም ከከፍታ ላይ መውደቅ፣ የኤሌክትሪክ አደጋ፣ የእቃዎች መውደቅ፣ የግንባታ መዋቅር ችግር እና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች በቂ ስልጠና አለመውሰድ እንዲሁም፤ የግል ደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎችን ያለመጠቀም ችግር ቀዳሚ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የቁጥጥር ችግር፣ ለደህንነት በቂ የሆነ በጀት አለመመደብ እና ሕግ የማስከበር ችግር ተጠቃሽ የአደጋ መንስኤዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት የሱፍ መሀመድ (ኢ/ር) በበኩላቸው፤ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ አደጋዎችን መቀነስ ይቻል እንደነበረ አንስተዋል።

በዚሁ አግባብም አደጋዎች የሚበራከቱት አብዛኞቹም ትኩረት ባለመስጠት እንደሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም የተጠናከረ ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ አንስተው፤ በግንባታ ሳይቶች ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቀነስ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ