ጥቅምት 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የኢትዮጵያን ዘመናዊነት የሚያፋጥን አዲስ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ስምምነት መፈራረማቸውን የኢፌዲሪ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በሩሲያ ፌዴሬሽን ያደረጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እና ሌሎች የሩሲያ ባለስልጣናት ጋር በትናንትናው ዕለት ተወያይተዋል።

በዚህም "የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን በሚመለከት ወደፊት በሚሄድበት መንገድ" ዙሪያ፣ በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ትብብር በማሳደግ እና በሩሲያና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን "ጥልቅ ታሪካዊ ትስስር" በማጠናከር ላይ ያተኮረ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

ከውይይታቸው በኋላም ከሞስኮ ጋር አዲስ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የሃይል ላኪ ለማድረግ ትልቅ ዕርምጃ መሆኑን በጋራ በሰጡት መግለጫ ይፋ አድርገዋል።

ይህ "ትልቅ ምዕራፍ" ነው የተባለለት እና በ'ኒውክሌር የድርጊት መርሃ ግብር' ሥር ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር የተፈራረመችው አዲሱ የኒውክሌር ጣቢያ ግንባታ ስምምነት፤ ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ የምታደርገውን ሽግግር እና ዘመናዊነት በከፍተኛ ሁኔታ ያፋጥነዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህም ኒውክሌርን እና የውሃ ሀይልን በማጣመር የቴክኖሎጂ ፈጠራን እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይአይ) እድገትን በአህጉሪቱ ለማራመድ ያለመ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በሃይል ትብብር እና በጋራ የቴክኖሎጂ ግስጋሴ ቀጣናዊ ውህደትን ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲል ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በሩሲያ በመጀመሪያ ቀን ቆይታቸው ከሩሲያ አቶሚክ ኤጀንሲ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ተገልጿል።

መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም ኢትዮጵያና ሩሲያ በኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ