መስከረም 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በጉራጌ ዞን 78 በመቶ የሚሆኑት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም ለአሐዱ አስታውቋል።

በተመሳሳይ 40 በመቶ የሆኑትን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ በዘንድሮው የ2018 በጀት ዓመት 600 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ፣ በጉልበትና በቁሳቁስ በማሰባሰብ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻል እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ኃላፊው ባለፉት ሁለት ዓመታት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በተሰሩ ሥራዎች የደረጃ ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ ገልጸዋል።

በ2018 በጀት ዓመትም በተመሳሳይ 'አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ' በሚል ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ መርሃግብር አማካኝነት፤ ከቅድመ አንደኛ እስከ 8ኛ ክፍል 78 ሚሊዮን ብር ሃብት ለማሰባሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት ከ300 ሺሕ በላይ የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሐፍት በማሳተም ለተማሪዎች ለማዳረስ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ኃላፊው በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ ተማሪዎችን ለማብቃት፣ ቤተ ሙከራና ቤተ-መጽሐፍት ለማጠናከር እንዲሁም የትምህርት ብክነት ለመከላከል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ 34 ሺሕ የማጣቀሻ መጽሐፍት በመግዛት እና ከ11 ሚሊዮን በላይ ሃብት በማሰባሰብ ቤተ-ሙከራ የማደራጀት ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በ2018 በጀት ዓመት 600 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ፣ በጉልበትና በቁሳቁስ በማሰባሰብ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻል እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል በዘንድሮ ዓመት በ276 አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት አመራር ሪፎርም እንደሚደረግ የገለጹት የትምህርት መምሪያው ኃላፊ፤ ይህም የትምህርት አመራር ሪፎርም ባለፈው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

አክለውም በ2017 ዓ.ም በተደረገው ሪፎርም በርካታ የትምህርት አመራሮች ለቦታው መስፈርቱን ያሟሉ ተወዳድረው እና ተፈትነው በቦታው መመደባቸውን ተናግረዋል።
ነገር ግን ባለፈው ዓመት ምደባ ወቅት ደረጃቸውን ያሟሉ በቂ ተወዳዳሪዎች ማግኘት ስላልተቻለ በተጠባባቂ የትምህርት አመራር የቆዩ እንዳሉ አንስተዋል።

ሆኖም በዘንድሮው ዓመት የትምህርት አመራር ሪፎርም ባልተደረገባቸው በሁሉም ደረጃ ያሉ 273 ትምህርት ቤቶች ዳግም ሪፎርም ተደርጎ ለቦታው በሚመጥኑ አመራሮች ይተካሉ ብለዋል።

"ባለፈው ዓመት ለተመዘገበው የትምህርት ውድቀት ተጠያቂው የትምህርት አመራሩ ነው" ያሉት ኃላፊው፤ ሪፎርሙ የሚደረገው በርዕሰ መምህራን፣ በምክትል ርዕሰ መምህራን እና በሱፐር ቫይዘሮች ላይ እንደሆነም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ