ጥቅምት 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ለታሪክ ኢትዮጵያ የሬድዮ አድማጮችና የሚዲያ ተከታታዮች ማህበር፤ በሸገር ከተማ በሚገኝ ማረሚያ ቤት በመገኘት 100 ሺሕ ብር የሚያወጡ የተለያዩ መጻሕፍቶችን በስጦታ መልክ አበርክቷል።

የማህበሩ ዋና ፅሐፊ የሆኑት አቶ ግሩም የኮተቤው፤ ማህበሩ ለትርፍ ያልተቋቋመና ሕጋዊ ሰውነት ተሰጥቶት የሚቀሳቀስ ማህበር መሆኑን ገልጸው፤ የተመሠረተበት አላማ ዜጋን በእውቀት መገንባት ነው ብለዋል።

Post image

ይህንን ታሳቢ በማድረግ ደግሞ ከ100 ሺሕ ብር በላይ ግምት ያላቸውና ከ1 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ መጻሕፍቶችን በሸገር ከተማ ማረሚያ ቤት ለሚገኙ ታራሚዎች ድጋፍ ማድረጉን ለአሐዱ አስታውቀዋል።

"መጻሕፍትን ለማንበብ ጊዜና ቦታ መምረጥ አያስፈልግም" ያሉት አቶ ግሩም፤ "እናም ይህን ታሳቢ በማድረግ በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጎደኞቻቸውና በአጠቃላይ ከተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች ተገለው የፍርድ ውሳኔቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ታራሚዎችን መደገፍ የግድ ይላል" ሲሉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የሸገር ከተማ ማረሚያ ቤት ሃላፊ የሆኑት ኮሚሽነር ዋጋሪ ጫላ በበኩላቸው፤ ማህበሩ በሸገር ከተማ ለሚገኙ ታራሚዎች ላደረገው የመጻሕፍት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

"መጻሕፍት ማንበብ ትውልድን የሚቀርፅ ነው" ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በተለይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አጥፍተው የእርምት ጊዜያቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ታራሚዎች፤ እንዲያነቡ እገዛ ማድረግ በእስር ቤት ቆይታቸው ሥነ-ምግባራቸውን እንዲያሳድጉ ትልቁ ድርሻ አለው" ሲሉ ለአሐዱ አስታውቀዋል።

Post image

ለታሪክ ኢትዮጵያ የሬድዮ አድማጮችና የሚዲያ ተከታታዮች ማህበር ከተቋቋመ አራት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ 30 አባላትን በውስጡ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

የማህበሩ ዋና ፅሐፊ አቶ ግሩም፤ ማህበሩ የራሱ የሆነ ህግ ደንብን መሰረት በማድረግ እንደሚተዳደር ገልጸዋል።

አክለውም ማንኛው ግለሰብ ወደ ማህበሩ ሲቀላቀል በወር ክፍያው 20 ብር ብቻ መሆኑን አስረድተው፤ በተዘዋዋሪ የትኛውም ግለሰብ ከማህበሩ በገዛ ፍቃዱ የመልቀቅ መብቱ የተጠበቀ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ