ጥቅምት 21/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነትን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረችበት ከመስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ፤ በርካታ ምርቶች በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ወደ አባል ሀገራት መላክ መጀመራቸው ተገልጿል።

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ ለሐዱ እንዳስታወቁት፤ ከተላኩት የመጀመሪያ የወጪ ንግድ ምርቶች መካከል ስጋ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቡና እና ጥራጥሬ እህሎች ይገኙበታል።
ከእነዚህ ምርቶች ወደ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሶማሊያና ጅቡቲ መላካቸው ተጠቅሷል።
ምርቶቹ በአብዛኛው የተጓጓዙት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ አማካኝነት ሲሆን፤ አየር መንገዱ ለነፃ ንግድ ቀጠናው ትግበራ ትልቁን ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነትን ከፈረሙት 54 ሀገራት መካከል፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ 28 ሀገራት ድንበሮቻቸውን በመክፈት የትግበራ እርምጃ መውሰዳቸውን አቶ ወንድሙ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያም ስምምነቱን ለመተግበር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እና የትግበራ ስትራቴጂ ሰነድ ማዘጋጀቷን፣ የታሪፍ ወይም የቀረጥ መወሰኛ መጽሐፍ ማሳተሟን እንዲሁም፤ የሀገሪቷን የንግድ ሕጎች ከአባል ሀገራት ጋር ማስማማቷን እንደ ዋና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ጠቅሰዋል። ይህም ለንግዱ እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮችን ለማስወገድና በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲካሄድ ለማድረግ አስችሏል ብለዋል።
የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ እና 3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ጥቅል ሀገራዊ ምርት (GDP) በመያዝ፤ አባል ሀገራት የእርስ በእርስ ንግድ ግንኙነት እንዲፈጽሙ በማድረግ ግዙፍ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስበት መሆኑን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል። በዚሁ ኢኮኖሚ ውስጥ የኢትዮጵያ ተሳትፎም እየላቀ መምጣቱን ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ በነፃ ንግድ ቀጠናው አማካኝነት እስካሁን የተላኩትን ምርቶች በመጠን እና የተገኘውን ገቢ በሚመለከት ያለው መረጃ ትግበራው ገና አዲስ በመሆኑ፤ ቀሪ የሚላኩ ምርቶችን በመጨመር የማደራጀት ሥራ እየተሠራበት መሆኑን ለአሐዱ አስረድተዋል።
በቀጣይ ምርቶችን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪ በየብስ እና በሌሎች የትራንስፖርት አማራጮች ለመላክ መታቀዱንም አስታውቀዋል።
ከሚላኩት ምርቶችም ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ አልባሳት፣ የግብርና ምርቶች እንዲሁም እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች እንደሚገኙባቸው ተናግረዋል።
የንግድ ቀጠናው በኢትዮጵያ አምራችነት እንዲስፋፋ፣ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እንዲሁም ለአፍሪካ ሴቶችና ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት አክለዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
 
  
  
  
 