ጥቅምት 21/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከ25 ዓመታት በኋላ በተሻሻለው የኢትዮጵያ ግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ መሠረት ለግብርናው ዘርፍ አገልግሎት የሚውሉ 555 ትራክተሮች ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን የኢትዮጵያ የግብርና ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

የግብርና ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንድለ ሀብታሙ (ዶ/ር)፤ አዲሱ ፖሊሲ በሀገሪቱ የሚገኙ አርሶ አደሮችን፣ አርብቶ አደሮችን እንዲሁም የአትክልት ምርት አምራቾችን በብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

ፖሊሲው ዘርፉን ለማሳደግ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ድጋፍ እንደሚደረግ የገለጹም ሲሆን፤ የግብርና ምርት የሚያመርቱ አርሶ አደሮች በማሽን የታገዘ አሠራርን እንዲከተሉ ለማድረግ በዝቅተኛ ዋጋ ማስገባት እንደሚችሉ እና በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው" ብለዋል።

ባለፉት ጊዜያት ለግብርና ምርት የሚያገለግሉ ማሽነሪዎች ከቀረጥ የሚገቡ እንደነበር አስታውሰው፤ አዲሱ ፖሊሲ ግን ይህንን የሚያስቀር እና ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

Post image

ከ25 ዓመት በኋላ የተቀየረው አዲሱ የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ በዋናነት ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።

በዚህም ለግሉ ዘርፍ የግብርና ቴክኖሎጂ፣ ግብዓትና አገልግሎትን በማቅረብ፤ በቀጥታ ምርት ማምረት፣ ግብይትና እሴት ጭመራ አገልግሎቶች ላይ እንዲሳተፍ በማድረግ ዘላቂ ምርትና ምርታማነት ዕድገትን ለማምጣት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

555 ትራክተሮች ከቀረጥ ነፃ መግባታቸውም አዲሱን ፖሊሲ ለማሳካት የግል ባለሀብቱን የማበረታታት አንድ አካል ነው ተብሏል፡፡

በ1994 ዓ.ም የወጣው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ 'የእንስሳትና የተፈጥሮ ሃብት ልማት እንዲሁም የግብርና ፋይናንስ አቅርቦት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ላይ ትኩረት ያላደረገ ነው' በሚል፤ ፖሊሲው በአዲስ መልክ መዘጋጀቱ የሚታወስ ነው፡፡

ሚያዚያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 31ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረትም፤ የተሻሻለው "የኢትዮጵያ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ" ፀድቆ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ