ጥቅምት 18/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትስዊች አክሲዮን ማህበር ዓመታዊ ገቢው 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መድረሱን በዛሬው ዕለት ባከናወነው በ12ኛው የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አስታውቋል።
ኩባንያው በዛሬው ዕለት በሸራተን አዲስ ሆቴል ባከናወነው የባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ፤ በባለፈው በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈጻጸም፣ ገቢ እና የፕሮጀክት አተገባበር ላይ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጿል።
የኢትስዊች አክሲዮን ማህበር ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሰሎሞን ደስታ በመድረኩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ "ኩባንያው በሀገሪቱ ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የክፍያ ሥነ-ምህዳር እንዲኖር በማድረግ ረገድ በባለፈው በጀት ዓመት ጉልህ እድገት አሳይቷል" ብለዋል።

በዚህም ኩባንያው በዓመቱ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ ማስመዝገቡን የገለጹ ሲሆን፤ በዚህም ከታክስ በፊት 1 ነጥብ 42 ቢሊዮን ትርፍ አስመዝግቧል ብለዋል።
ይህም የትርፍ ገቢ ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ34 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ነው የገለጹት።
በተጨማሪም የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል እስከ ሰኔ ወር ድረስ ወደ 2 ነጥብ 56 ቢሊዮን ማደጉን የገለጹት አቶ ሰለሞን፤ ይህም ባለአክሲዮኖች ለኩባንያውን እድገት እና ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትን ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
እንዲሁም አክስዮን ማህበሩ ከ287 ሚሊየን በላይ ግብይቶችን በመፈጸም ከ740 ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር መደረጉን ገልጸዋል።

ከዚህ የገንዘብ ዝውውር ውስጥ ከ577 ቢሊየን ብር በላይ የሚሆነው ከአንድ የፋይናንስ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም በተደረገ የገንዘብ ማስተላለፍ የተዘዋወረ ገንዘብ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 158 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ነው ያስታወቁት።
በተጨማሪም የ1 ሺሕ ብር አክሲዮን የትርፍ ድርሻ ወደ 486 ብር ማደጉን የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሩ፤ የኩባንያው አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታል ከ2 ቢሊየን 500 ሚሊየን ብር በላይ መሻገሩን ተናግረዋል።

ኢትስዊች በሁሉም ባንኮች ማለትም በግል እና በመንግሥት ባንኮች እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚተዳደር ሲሆን፤ በፋይናንስ ተቋማት መካከል ትብብር ለመፍጠር፣ የሀገር ውስጥ የክፍያ ስርዓትን ለማሳለጥ እና በብሔራዊ የክፍያ ስርዓት መካከል የእርስ በርስ የገንዘብ ዝውውር ስርዓት እንዲኖር የማድረግን ሃላፊነት ይዞ በመስራት ላይ ይገኛል።
በተጨማሪም ያልተቋረጠ እና ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን አገልግሎቶችን በመላ ሀገሪቱ ላሉ የፋይናንስ ተቋማት ለማድረስ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ኩባንያው በተያዘው በጀት ዓመት የአገልግሎት ጥራቱን ለማሻሻል፣ መሠረተ ልማቶችን ለማሻሻል፣ ቀጣይ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ፣ አዳዲስ ዲጂታል አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ እና ድንበር ተሻጋሪ የክፍያ ሽርክናዎችን ለማጠናከር እንደሚሰራ አስታውቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ