ጥቅምት 18/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የትምህርት ስርዓቱ ከሰኞ እስከ እሁድ መደረጉ በትምህርት አቀባበል ላይ የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት እንደሚቀንስና ስሜት አልባ የመሆን ችግር እንደ ሚያስከትል እና ከፍተኛ የሆነ የሥነ-ልቦና ጫና እንደሚያሳድር የትምህርት ባለሙያዎች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሒሳብ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት እና የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሒሳብ ትምህርት ሃላፊ ሳሙኤል አሰፉ (ዶ/ር)፤ ተማሪዎች ያለ እረፍት የሚማሩ ከሆነ ትምህርት የመቀበል ፍላጎታቸው እንደሚቀንስ እና ትምህርን ከመማር ይልቅ እንደ ሸክም የመመልከት እድል ከፍተኛ መሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ይህን አሰራር እንዲወጣ ከማድረግ ባለፈ ምን አይነት ጉዳት ያመጣል የሚለው መታየት እንደነበረበት አንስተው፤ ተማሪዎች ከትምህርት ወደ ትምህርት ያለ እረፍት መዘዋወራቸው ዝግጁ ሆነው የመማር እድላቸው ዝቅተኛ እንደሚሆን አሳስበዋል።

ትምህርት ማለት ውጤታማ መሆን እንደሆነ በመግለጽም፤ ውጤታማነቸውን እንደሚቀንስ፣ ተማሪዎች የድካም ስሜት እንዲሰማቸው እንዲሁም ትምህርት እንዲጠሉ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።

ተማሪዎች ከትምህርት የሚያገኙት እውቀት ብቻ በቂ አለመሆኑን አንስተው፤ ከማህበረሰብ ጋር ግንኙነት ማድረግ እንዳለባቸውና ይህ ከግምት መግባት እንደነበረ አስታውቀዋል።

ይህ ችግር እንዲከሰት ያደረገው የተማሪዎች ፈተና ማጠናቀቂያ ግንባት ወር ብቻ መሆኑ እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ሳሙኤል፤ ያለውን ጊዜ በማጥበብ ከመስራት ባለፈ ከክረምት ጊዜ የአንድ ወር ጊዜ በመውሰድ የፈተና ጊዜው እንዲራዘም ቢደረግ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ሌላኛው የትምህርት ባለሙያና የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አካቶ ትምህርት ባልደረባ ጥሩሰው ተፈራ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ ይህ አሰራር በልጆች ላይ የሥነ-ልቦና ጫና እንደሚያሳድር ተናግረዋል።

ተማሪዎች በቂ ዝግጁት እንዲያደርጉ የወጣ መርሃ ግብር ሊሆን እንደሚችል አንስተው፤ ተማሪዎች ያለ እረፍት እንዲማሩ መደረጉ ጫና እንደሚኖረው እና ተማሪዎች እረፍት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም የስሜት መዛባት እና ከወላጆቻቸው ጋር በቂ ጊዜ እንዲያሳልፉ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከሰሞኑ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በማሰብ፤ በከተማዋ የሚገኙ የግልና የመንግሥት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፤ ከሰኞ እስከ አርብ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት እንዲማሩ ጥዋት በአንድ ሰዓት ወደ ትምህትት ቤት እንዲገቡ በተጨማሪም በተመረጠ ትምህርት ቤት አንድ ላይ ቅዳሜና እሁድ እንዲማሩ የሚያስገድድ መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ