የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጥቅምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም. መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተገኙበት በተካሄደው በዛሬው ጉባዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ወቅታዊ፣ ሀገራዊ እና ቀጠናዊ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የዛሬው ስብሰባ የተካሄደው በ2008 ዓ.ም. በወጣው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ መሰረት ነው፡፡ የሥነ-ምግባር ደንቡ ፕሬዝዳንቱ የፌዴራል መንግሥትን ዕቅድ አቅርበው የዓመቱን የፓርላማ ሥራ ከከፈቱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ተገኝተው ማብራሪያ እንዲሰጡ ይደነግጋል።
በዚህም መሠረት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የፌዴራል መንግሥትን የዚህ ዓመት ዕቅድ ለተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት ካቀረቡ በኋላ የዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ተጠባቂ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ በንባብ ባሰሙት ዕቅድ ላይ ገለልተኛና ሕዝባዊ ብሔራዊ ተቋማትን መፍጠር፣ በየቦታው የሚታዩ ግጭቶችን ማስቆም፣ ለሕዝብ የቀረበና ለሕግ የታመነ አስተዳደር መፍጠር እና መንግሥት የዜጎችን ዋስትና የሚያስጠብቅ የፍትሕ ሥርዓት መዘርጋት የ2018 ዓ.ም. የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑ ገልጸው ነበር።
ምክር ቤቱ 5ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት በዚህ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመንግሥትን ዕቅድ በሰፊው አብራርተዋል።
በተጨማሪም ቀደም ብለው እጃቸው ላይ ለደረሱት ጥያቄዎች እና አስተያየቶች መልስ፣ ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዋል።
ከምክር ቤት አባላት በርካታ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል፤ 'የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር መንግሥት ተደጋጋሚ ሥራዎችን ቢሠራም፤ ከደመወዝ ጭማሪ በኋላ ነጋዴዎችና የቤት አከራይ ማኅበረሰቦች በዘፈቀደ ጭማሪ እያደረጉ በመሆኑ እነሱን ለመቆጣጠር ምን እየተሠራ ነው?' የሚለው አንዱ ጥያቄ ነው።
በተጨማሪም 'በትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እና ቀጣይ እጣ ፈንታ፣ በክልሉ ያሉ አንዳንድ አካባቢዎች ሰላምን ለማወክ እየሠሩ ያሉ አካላትን መቆጣጠር አልተቻለም?' የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
'የባሕር በር ጥያቄ ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር እንዴት ይታያል?' እንዲሁም፤ 'የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም ይህ ጉዳይ ሰላማዊና የህልውና ጥያቄ እንደሆነ እንዲገነዘብ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ቢገለጹ?' የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበዋል።

የዘመናት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ የሆነውን የቀይ ባሕር ጉዳይ የሚቃወሙ "ባንዳዎች" አሉ ሲሉ የወቀሱት የምክር ቤት አባላት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሀገሪቱ ላመጡት ለውጥ ከፍተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሌላው በምክር ቤት ጥያቄ ያቀረቡት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን ፓርቲ አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ናቸው።
ዶክተር ደሳለኝ ከጥያቄያቸው አስቀድመው የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ነገር ግን ከሕዳሴ ግድብ ጋር 4 ሌሎች ግድቦች አብረው እንዲገደቡ ታቅዶ እንደነበር ተናግረዋል።

በመሆኑም ቢያንስ ከሦስት አንዱን ግድብ መሥራት ቢጀመርና በእሳቸው ጊዜ መሠረት ድንጋይ ቢጣል፣ ቀጣዩ ትውልድ እንዲጨርሰው ሐሳብ አቅርበዋል።
ጥያቄዎቻቸውን ሲቀጥሉም፤ ጥያቄዎች ማቅረብ እንደ 'ጨለምተኝነት' እንዳይቆጠር ቀደም ሲል የተሰጣቸውን ምላሽ አስታውሰዋል።
በጥያቄያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኦሮሚያና አማራ ክልል ካለፈው ዓመት ወዲህ በግጭቶች የተጎዱና ሕይወታቸው ያለፈ ዜጎችን ትክክለኛ ቁጥር እንዲገልጹላቸው ጠይቀዋል።
በተጨማሪም በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞች ባሉበት ሁኔታ ቀጣዩ ምርጫ ተዓማኒ ይሆናል ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል። የቀይ ባሕር ጉዳይ የውስጥ ጉዳይን ማስቀየሻ ነው የሚል ሥጋት መኖሩን አንስተዋል። "ለመሆኑ መንግሥት በቀይ ባሕር ጉዳይ የሄደበትን ያህል ርቀት የውስጥ ጉዳዮችን ለመፍታት ለምን አይጠቀምበትም?" ሲሉም ጥያቄያቸውን አጠናቀዋል።
ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከምላሻቸው አስቀድመው ያለፈው ዓመት “መንግሥት ትልልቅ ጉዳዮችን ያሳካበት ነው” ብለዋል፡፡ ለስኬቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ ይህን ስኬት ላመጡ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመቀጠል በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ከመጨረስ ጋር በተያያዘ ስኬቶች መኖራቸውን ተናግረዋል። "በተለይም የመንገድ ፕሮጀክትን በተመለከተ 346 የተጀመሩ ፕሮጀክቶች አሉ" ብለዋል።
ይህ በ1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር በጀት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ጦርነቶች፣ ግጭቶችና የፕሮጀክቶች ስፋት አንጻር በሚጠበቀው ልክ ላይጠናቀቅ እንደሚችል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
ከተረጂነት ጋር በተያያዘም በተነሳው ሐሳብ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ከተረጂነት ተላቀናል አንልም" ብለዋል። ረጂዎች ስንዴ ትተው ትምህርት ቤትና መንገድ የመሰሉትን ቢሠሩ ደስ እንደሚላቸውም አመልክተዋል።
"ከተረጂነት ለመላቀቅ ዋነኛው ሥራ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለፉት 30 ዓመታት ሰላም የነበራት ትግራይ አሁንም ከስንዴ ልማት መገላገል አለመቻሏን አስረድተዋል።
በኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ ማጠቃለያ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ "ኢትዮጵያ በ2032 ዓ.ም. ከአፍሪካ ሁለተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ትሆናለች" ብለዋል። በመቀጠልም በ2036 ዓ.ም. ደግሞ ኢኮኖሚዋ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃ ይሆናል ሲሉ ለምክር ቤቱ ቃል ገብተዋል።
"ኢትዮጵያን የምንመራው እንደ 'ላዳ' ሹፌር ሳይሆን እንደ 'ባስ' ሹፌር ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ጉዟችን በሕልም ነው የሚመራው" ሲሉ ገልጸዋል።
ሠላምን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ኢትዮጵያን መገንጠልም ሆነ መጠቅለል እንደማይቻል ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ከሌለው፣ ምርጫ ከማያደርግና ሕገ-መንግሥት ከሌለው አካል ተልዕኮ ተሸክመው የባንዳነት ሥራ የሚሠሩ አካላትን ወርፈዋል።
ይሁን እንጂ መወያየት የሚፈልግ ማንኛውም አካል ከመጣ መንግሥታቸው ለመወያየት ክፍት መሆኑን አብራርተዋል። "እኔና ጌታቸው ረዳን አንድ ላይ የሚያመጣ አካል መንግሥት አይወያይም ብሎ ማሰብ አይገርምም ወይ?" ሲሉ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልልን በተመለከተ፣ "የፕሪቶሪያን ስምምነት እንዳይከበር እንቅፋት እየሆኑ ያሉት አካላት መንግሥትን መክሰስ አይገባቸውም" ሲሉ ገልጸዋል። "ህወሓት አሁንም ወደ ሰላማዊ መንገድ መምጣት አለበት" ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ፣ በጦርነት የሚመጣ ለውጥ የለም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ምርጫን በተመለከተ የተቃዋሚ ፓርቲ አካላት ምቹ ሁኔታ አለመኖሩን በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል። ይህንን በሚመለከት ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ "ኤርትራ ምርጫ አይካሄድ ስላለች ምርጫ መከናወን የለበትም የሚሉ ኃይሎች አሉ" ብለዋል። ይሁን እንጂ 7ኛው ዙር ምርጫ በእርግጠኝነት ይካሄዳል።
ብዙ ድምፆች እዚህ ምክር ቤት ይገባሉ ሲሉም ተስፋቸውን ገልጸዋል። ያለፈውን ምርጫ እየተዋጉ እንዳካሄዱት አስታውሰዋል። በ1992 ዓ.ም. ከኤርትራ ጋር እየተዋጉ ምርጫ ማከናወናቸውን አስረድተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ