ሕዳር 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትስዊች እና ጀነሲስ አናሊቲክስ መካከል የ15 ዓመት እና የአምስት ዓመት መሪ እቅድ በመቅረጽ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ ፈጠራ የታከለበት፣ አስተማማኝ እና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የዲጂታል የገንዘብ ዝውውር ስርዓቱን የሚያጠናክሩ መፍትሄዎችን ለፋይናንስ ተቋማት ለማቅረብ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

Post image

የተደረገው ስምምነት ዓለም አቀፍ አሰራሮችን በመከተል በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራ ውስጥ ትልቅ መንገድ ስለመክፈቱ ተጠቅሷል።

ስምምነቱ ሸማቾችን በተቀላጠፈ የዲጂታል ሥርዓት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር የበለጠ ለማጠናከር ካላቸው የጋራ ቁርጠኝት በመነሳት መሆኑንም በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ወቅት ተብራርቷል፡፡

በተደረሰው አጋርነት መሰረት ኢትስዊች እና ጀነሲስ አናሊቲክስ የተለያዩ የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት አቅሞችን ለማሳደግ እና ለመተግበርም አብረው የሚሰሩ ይሆናል።


ዲጂታል የገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱ ከፈጣን ኔትዎርክ ጋር እንዲተሳሰር እና ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቢዝነሶችም ዓለም አቀፍ ክፍያዎችን እንዲቀበሉ እና ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጥም ለማድረግ እድሎችን ለማስፋት እንደሚያስችል ተገልጿል።

በስምምነት መርሐ ግብሩ ላይ የኢትስዊች እና የጀነሲስ አናሊቲክስ ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ የቦርድ አባላት እና ሠራተኞች ተገኝተዋል።

ከቀናቶች በፊት ኢትስዊች እና ማስተርካርድ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የክፍያ አቅሞችን ለማስፋት የሚያስችል ስምምነት መፈራሙ ይታወሳል።

የክፍያ ጥያቄዎችን በባንኮች፣ በካርድ ኔትወርኮች እና በክፍያ አገልግሎት አቅራቢዎች መካከል የሚያገናኝ ስርዓት ላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ኢትስዊች ከማስተርካርድ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የክፍያ አቅሞችን ለማስፋት የሚያስችል ስምምነት መሆኑ መገለጹ አይዘነጋም።

ከዚህ ቀደም ተቋማት በተለይም ባንኮች ከማስተር ካርድ ጋር ተገናኝተው መስራት የጀመሩ ቢሆንም አሁን ግን በኢትስዊችበኩል በጋራ ዓለም አቀፍ የክፍያ ስርዓት ውስጥ መሳተፍ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩ ተገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ