መስከረም 19/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) መስከረም 24 እና 25 2018 ዓ.ም የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል አስመልክቶ የተደረገውን ቅድመ ዝግጅት እና የመገናኛ ብዙኃን ሚናን ላይ ትኩረቱን ያደረገ የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት ተካሄዷል፡፡
"ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ቃል በዓሉ እንደሚከበር የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው በመግለጫው ላይ በዓሉ ፈጣሪ እና ፈጥረት የሚመሰገንበት እንደመሆኑ የሕዝብ ባህል እንዲሆን መስራት እንደሚያስፍልግ ገልጸዋል፡፡
ኢሬቻ የወንድማማችነት የሰላም፣ የፍቅር መገለጫ መሆኑን አንስተው፤ ያለጾታ፣ ሐይማኖት እና የብሄር ልዩነት የሚከበር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ባህል እና እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር በማድረግ ለትውልድ እንዲተላለፍ መስራት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

"ኢሬቻ ወቅት የሚፈራረቅበት የተስፋ ምልክት የኦሮሞ ሕዝብ አንድነት ምልክት ነው" ያሉት አቶ ሀይሉ፤ የፖለቲካ እና የሐይማኖት ልዩነት ቢኖርም ውበትን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በዓሉ ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳለው አንስተው፤ በዓሉ በሚከበርበት ወቅት የትኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡
በዓሉን እና እሴቱን ከሚያጠለሹ አሉታዊ አስተሳሰቦች በቆጠብ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ፤ ከዚህ ቀደም የነበረው የመገኛኛ ብዙኃን ዘገባ ላይም ግምገማ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በግምገማውም 'ኢሬቻ ተከበረ' ከማለት ባለፈ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ተጨማሪ ዘገባዎችን በመስራት በኩል በመገናኛ ብዙኃን ላይ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ መስከረም 24 እና 25 2018 ዓ.ም በሚከበረው የኢሬቻ በዓል አስመልክቶም፤ በእውቀት ላይ የተመሠረተ፣ ስለ በዓሉ ግንዛቤ መስጠት የሚችል እንዲሁም በበዓል አከባበሩ ዙሪያ እውቀት ያለውን እንግዳ በመጋበዝ ሰፋ ያሉ ዘገባዎችን መስራት ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
መረጃን በመስጠት በኩል በክልሉ በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት እንደሚሰራም የኮሙኒኬሽን ኃላፊው ለአሐዱ አስታውቀዋል፡፡
ኢሬቻ በዓለም አቀፉ የቅርስ መዝገብ (ዩኔስኮ) ላይ እንዲመዘገብ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ሌላው በመድረኩ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምብሩ በበኩላቸው፤ በዓሉ በብዙ መልኩ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ለበዓሉ ሌላ ስያሜ መስጠት የተሳሳተ እና ተገቢ እንዳልሆነ አንስተው፤ ያለምንም ልዩነት የሚከበር በዓል እንደመሆኑ ባህል እና እሴት ወንድማማችነትን የሚያጠናክሩ ጉዳይዎች ላይ ማተኮር እና መስራት እንደሚያስፍልግ ጠቁመዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ