መስከረም 19/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አባል ነኝ በማለት በሀሰተኛ መታወቂያ ሰዎችን በማስፈራራት እያገተ ገንዘብ ሲቀበል የነበረን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።

ዳዊት ጥላሁን ወይም ምንተስኖት ጥላሁን የተባለው ግለሰብ ሀሰተኛ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መታወቂያ በመጠቀም 'የተቋሙ ሰራተኛ ነኝ' በማለት ሰዎችን በማገትና በማስፈራራት ገንዘብ እንደሚቀበል ከህብረተሰቡ የመጣን ጥቆማ መነሻ በማድረግ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በጥምረት ባደረጉት ክትትል ግለሰቡን መስከረም 16 ቀን 2018 ዓ/ም በቁጥጥር እንዲውል ማድረጋቸው ነው የተገለጸው።

Post image

ተጠርጣሪው ከሜክሲኮ ወደ ጋርመንት በታክሲ ተሳፍራ የምትሄድን የግል ተበዳይን ሳሮን ተስፋዬን 'ደህንነት ነኝ' በማለት በማስፈራራት እና በመደብደብ ጉዳት ያደረሰባት መሆኑን የግል ተበዳይ በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨቷ ይታወቃል።

Post image

ግለሰቡ በግል ተበዳይ ላይ ባደረሰው ጉዳት በሕግ የሚጠየቅ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።

ግለሰቡ በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት ሀሰተኛ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መታወቂያ እንደተገኘበት ፖሊስ አስታውቋል።

በግለሰቡ በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የተፈጸመበት ግለሰብ እና ስለ ግለሰቡ ማንኛውም መረጃ ያለው ሰው ለአዲስ ለአበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደረግ እና 'የጸጥታ አካላትና አባል ነን' በማለት የሚያስፈራሩና ተጽዕኖ የሚያሳደሩ ግለሰቦች ሲያጋጥሙት በወቅቱ ለፖሊስ እንዲያሳውቅ መልዕክት ተላልፏል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ