መስከረም 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በመዲናዋ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ የጉልበት ብዝበዛ ወንጀል ሲፈፀምባቸው የነበሩ 18 ሕጻናትና ታዳጊዎችን ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው ኦ አቤም ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ የሰባት ዓመት ታዳጊ በመንገድ ላይ እያለቀሰ ሳለ፤ ለምን እንደሚያለቅስ ሲጠየቅም ለሥራ የተሰጠው ሚዛን እንደጠፋበትና አሰሪዎቹም ቤት እንደማያስገቡት ይናገራል።

Post image

የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከታዳጊው የተቀበለውን መረጃ መነሻ በማድረግና ተገቢውን ክትትል በማከናወን በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ቦታው ቻይና ካምፕ አካባቢ ከሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ፤ ዕድሜያቸው ከ7 እስከ 13 ዓመት የሆኑ 18 ሕጻናትና ታዳጊዎችን ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር ሊያውል መቻሉን አስታውቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ እነዚህኑ ሕጻናትና ታዳጊዎች ክልል ድረስ በመሄድ ከቤተሰቦቻቸው ላይ 'እናስተምራቸዋለን' ብለው በማምጣት ቆሎ፣ ሶፍት እንዲሁም ሚዛን በማሰራት ከእያንዳንዳቸው በቀን ከ150 እስከ 300 ብር ገቢ እንዲያስገቡ ከማድረጋቸውም በላይ የወንጀል አፈጻጸሞችን (የመኪና ስፖኪዮ አነቃቀል) ያስተምሯቸው እንደነበርም የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

Post image

በግለሰቦቹ ላይ ተገቢው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ያስታወቀው ፖሊስ፤ በዐቃቤ ሕግም በኩልም ክስ እንደተመሠረተባቸው አስታውቋል፡፡

ሕፃናትን ለእድሜያቸው በማይመጥን የጤና፣ የእድገት፣ የማኅበራዊና ስነ-ልቦናዊ ደህንነታቸውን የሚጎዳና ለሕይወታቸው አስጊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲሰሩ ማድረግ የህግ ተጠያቂነት የሚያስከትል ተግባር መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውሷል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ መሰል ድርጊቶች ሲያጋጥሙት በአቅራቢያው ለሚገኝ የፀጥታ ተቋም መረጃ በመስጠት በሕጻናት ላይ የሚደርስ የጉልበት ብዝበዛን መከላከል ይገባል ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ