መስከረም 30/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቆጣሪ ምርመራ አሠራርን በማዘመን ግልፅነትን፣ ተጠያቂነትን እና ተአማኒነትን ለማስፈን ያለመ ዘመናዊ መተግበሪያ ከነገ ጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ እንደሚያውል አስታውቋል።

መተግበሪያው የቆጣሪ ምርመራ ሥራ መረጃዎችን በዲጂታል ሲስተም እንዲመዘገቡ ያስችላል። ይህም ከፍጆታ ክፍያ እና ከኃይል ብክነት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን በመቀነስ፣ ለደንበኞች ግልፅነትን እና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ አሠራር ለመፍጠር ይረዳል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በዛሬው ዕለት ለአሐዱ በላከው መግለጫ እንዳብራራው ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው መተግበሪያ፤ ከዚህ በፊት በማኑዋል ይመዘገብ በነበረው መረጃ ላይ የሚስተዋሉ የምርመራ መረጃ ክፍተቶችን ያስቀራል።

መተግበሪያውን በቀላሉ በእጅ ስልክ ላይ በመጫን የቆጣሪ ምርመራ መረጃዎችን ለመመዝገብ ያስችላል።

Post image

በተጨማሪም መረጃዎችን ከጂፒኤስ እና ሥራው ከተከናወነበት ሰዓት ጋር በማገናኘት የሚመዘግብ ሲሆን፤ ደንበኞች ቅሬታ ሲኖራቸው በግልፅ እና በተደራጀ መረጃ ተመስርቶ ውሳኔ ለመስጠት እንደሚችል አብራርቷል፡፡

በሌላ በኩል የቆጣሪ ምርመራ ሲከናወን፤ በማን እንደተሠራ፣ ምን ግኝቶች እንደተገኙ፣ መቼ ምርመራው እንደተከናወነ እንዲሁም የተገኘው ግኝት እና የተወሰደውን እርምጃ ሁሉንም በሲስተም በአንድ ስክሪን ላይ ማየት የሚያስችል መሆኑን ገልጿል፡፡

ይህ ዘመናዊ መተግበሪያ ተቋሙ በአሠራሩ ላይ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለመፍጠር እንዲሁም፤ የደንበኞችን አጠቃላይ አገልግሎት ለማዘመን እያደረገ ያለውን ጥረት ይደግፋል ተብሏል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ