መስከረም 30/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የቬንዙዌላ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ማሪያ ኮሪና ማቻዶ የ2025 የኖቤል የሰላም ሽልማትን ማሸነፋቸውን የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ አስታውቋል።
የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ "እየጨመረ በመጣው ጨለማ ውስጥ የዲሞክራሲን ነበልባል የምትጠብቅ ሴት" ሲል የጠራቸው ማቻዶ፤ ከ20 ዓመታት በላይ ለፍትህ ነፃነት፣ ለሰብአዊ መብቶች እና ለሕዝባዊ ውክልና ሲሟገቱ የቆዩ ሲሆን፤ ለቬንዙዌላ ሕዝብ ነፃነት ሲሰሩም ዓመታትን አሳልፈዋል።

በዚህም የዲሞክራሲ መሳሪያዎች የሰላም መሳሪያዎች መሆናቸውን ያሳዩ፤ የዜጎች መሰረታዊ መብቶች የሚጠበቁበት እና ድምፃቸው የሚሰማበት የወደፊት ተስፋን የጣሉ ስለመሆናቸው ተገልጿል።
ማቻዶ ለነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ፣ ከጠብ መንጃ ይልቅ በምርጫ ሳጥን ስልጣን እንዲገኝ ለረጅም ዓመታት ትግል ማድረጋቸውንም ነው ኮሚቴው ያስታወቀው፡፡
በዚህም መሠረት የዘንድሮ የኖቤል የሰላም ተሸላሚዋ ማሪያ ኮሪና ማቻዶ፤ ከሜዳሊያ እና ምስክር ወረቀት በተጨማሪ የ11 ሚሊዮን የሲውዲን ክሮነር (1.2 ሚሊዮን ገደማ) ተሻላሚ ሆነዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ