መስከረም 30/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አስመጪዎች የጥገና እና ሰርቶ ማሳያ ወይም ጋራዥ ማቋቋም እንዳለባቸው የሚያስገድድ መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

የመመሪያውን ተግባራዊ መደረግ ተከትሎ ለአሐዱ ቅሬታቸውን ያቀረብ የኤሌትሪክ ተሽከርካሪ አስመጪዎች፤ መመሪያው ያሉትን አስመጪዎች ከገበያው ከማስወጣቱም ባለፈ፤ አዳዲስ አስመጪዎችም ወደ ዘርፉ እንዳይቀላቀሉ እንቅፋት ይሆናል ብለዋል፡፡

‎በቂና ብቁ ባለሙያ በሌለበትና በቂ የመኪና መለዋወጫ ባልተሟላበት ሁኔታ 'ሁሉም አስመጪዎች የሰርቶ ማሳያ እና የጥገና ክፍል ወይም ጋራዥ ያቋቁሙ' ቢባል እንኳን፤ በቂ የመሬት አቅርቦት አይኖርም ሲሉ አስመጪዎቹ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

Post image


አሐዱም የኤሌትሪክ ተሽከርካሪ አስመጪዎችን ቅሬታ በመያዝ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርን ጠይቋል።

‎በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የትራንስፖርት አገልግሎት እና ቁጥጥር አማካሪ አቶ አሰፋ አዲስ የጸደቀው መመሪያ ተግባራዊ አለመደረጉን ጠቅሰው፤ መመሪያው የሚጠቅመው በአስመጪዎችና በተጠቃሚዎች መካከል አስተማማኝ የሆነ ዋስትና እንዲኖር ነው ብለዋል፡፡

ይህም በዘርፉ ቀጣይነት ያለው ሥራ እንዲሰሩ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አስመጪዎች የብቃት ማረጋገጫ ወስደው ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ፤ መመሪያውን አክብረው መስራታቸው ግዴታ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

በኢትዮጵያ ከ400 በላይ ተቋማት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እያስመጡና እየገጣጠሙ መሆናቸውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ