ጥቅምት 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሕዝብ ማመላለሻ የከተማ አውቶብሶች ውስጥ በጉዞ ወቅት የሚደርስ ፆታዊ ትንኮሳን የሚመለከት ቅሬታ በተበዳዮች ቀርቦለት እንደማያውቅ፤ የአዲስ አበባ ከተማ፣ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት አስታውቋል።
በከተማ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ውስጥ ጾታዊ ጥቃት የሚፈጽሙ ጥፋተኞች ስለመኖራቸው ማኅበራዊ ሚዲያን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ሲነገር ቢደመጥም፤ የከተማ አውቶብስ አገልግሎቱ "ጥቃት ስለመፈጸሙ የሚገልጽ ምንም አይነት መረጃ ከተበዳዮች ደርሶኝ አያውቅም" ብሏል።

የተቋሙ የአገልግሎት ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ከበደ፤ "ችግሩ በመደበኛ ሪፖርት ባይቀርብም በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ውስጥ የሚፈጸም ጾታን መሰረት ያደረገ ትንኮሳን ጨምሮ ሌሎችንም ወንጀሎች ለመቆጣጠር እና ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ በአውቶብስ ውስጥ በተገጠሙ የደህንነት ካሜራዎች አማካኝነት ቁጥጥር ይደረጋል" ብለዋል።
አንድ አውቶብስ በአማካይ 70 ሰዎችን የመጫን አቅም ቢኖረውም፤ ከአቅም በላይ ተሳፋሪ በሚጫንበት ጊዜ የሚፈጠረው መጨናነቅ ተመሳሳይ ወንጀል ሊዳርግ ስለሚችል ማኅበረሰቡ ተመሳሳይ ወንጀሎችን በጋራ እንዲከላከልም ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
 
  
  
  
 