ጥቅምት 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ አሁንም በሕገ-ወጥ ሰፈራ ምክንያት ሥጋት ውስጥ ከሚገኙ ፓርኮች መካከል አንዱ መሆኑኔ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ለአሐዱ አስታውቋል።
ባለስልጣኑ በክልል ብሔራዊ ፓርኮች የተሰሩ የልማት ሥራዎች የፓርኮችን ጉዳት በመቀነስ የቆርኬዎችን ቁጥር መጨመራቸውን ገልጿል።
በዚህሞ በ"ስንቅሌ ቆርኬዎች መጠለያ" ብቻ በ2016 እና በ2017 ዓ.ም. 120 አዳዲስ የቆርኬ ግልገሎች ተራብተዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን፤ በአዋሽ፣ በባሌ ተራሮች እና በጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ እየተሠራ ያለው ሥራ ጥሩ ጅማሮ አሳይቷል።
ማኅበረሰቡ ከፓርኮቹ የሚያገኘው ገቢ ሲያድግ የሚደርሱ ጉዳቶች ይቀንሳሉ ሲሉሜ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
"የብዙዎቹ ፓርኮች ጥፋት የሚመነጨው ከ'እየኔነት' ስሜት ማጣት ጋር የተያያዘ ነው” ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ከፓርኩ ተጠቃሚ የሚሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ቁጥር ሲጨምር የፓርኮች ጉዳት እንደሚቀንስ አብራርተል።
የቆርኬዎቹ ቁጥር የቀነሰው ከሰው ሠራሽ ምክንያቶች በተጨማሪ፤ የተፈጥሮ ሚዛን መዛባትና የበይና ተበይ እንስሳት ቁጥር አለመመጣጠን ነው ተብሏል።

ይህንን ችግር ለማስቀረትም የፓርክ ጠባቂ ስካውቶች ድንኳን ተክለው ቆርኬዎቹን በልዩ ሁኔታ መንከባከባቸው፤ ከመጥፋት ተርፈው ለመራባታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፣ ቁጥራቸው እየቀነሰ ያለ የዱር እንስሳትን ቁጥር በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙትን እንሳቶች ቁጥር ለመጨመር በተሠራው ሥራ ውጤት መገኘቱ ተጠቁሟል።
ነገር ግን የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ አሁንም በሕገ-ወጥ ሰፈራ ምክንያት ሥጋት ውስጥ ነው ሲል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስጠንቅቋል።

የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ 6 ሺሕ 982 ኪሎ ሜትር ስኩየር ስፋት ያለው መጠለያ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት በተደረገ ቆጠራ 200 ዝሆኖች በመጠለያው ውስጥ እንደሚኖሩ ተረጋግጧል።
በመጠለያው ከዝሆኖች በተጨማሪ የቆላ አጋዘን እና ሌሎችን ጨምሮ 31 ዓይነት አጥቢ የዱር እንስሣት ያሉ ሲሆን፤ እንዲሁም ከ225 በላይ የአዕዋፍ እና 238 የእጽዋት ዝርያዎች ይገኛሉ።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
 
  
  
  
 