ጥቅምት 29/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር የወጪ ንግድን ለማከናወን በሚደረገው ሂደት ውስጥ ስጋት አለመሆኑን፤ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ፤ የገቢ ምርትን በመቀነስ የወጪ ንግድ ላይ ትኩረት በመስጠት በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ለአሐዱ ሬዲዮ ገልጸዋል።

ከእነዚህም ውስጥ የመንግሥት የውጪ ምንዛሬ አስተዳደር ስርዓት በገበያ እንዲመራ መደረግ አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ሂደት ግን አጠቃላይ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለወጪ ንግድ የሰላም መኖር እና ነፃ የሆነ እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑን በመግለጽም፤ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ የሰላም እጦት መኖሩን አክለዋል።

ነገር ግን የፀጥታ ችግር ያለባቸው ቦታዎች ላይ የወጪ ምርቶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለማድረግ፤ የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪ አካላት ጥበቃ የሚያደርጉበት አግባብ መኖሩን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት የወጪ ንግድን ሊያስተጓጉል የሚችል ተግዳሮት እና ስጋት እንዳልሆነ የገለጹም ሲሆን፤ ያን ያክል ምርቶች ላይ ችግር የሚፈጥርበት ሁኔታ አለመኖሩን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እስካሁን በብዛት ወደ ውጪ ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥ፤ የቅባት እህሎችና ጥራጥሬዎች፣ የአገዳ ሰብሎች፣ ቡና፣ ቅመማ ቅመም እና ጫት የመሳሰሉ የግብርና ውጤቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ጨርቃ ጨርቆችንና የቆዳ ውጤቶችን የመሳሰሉ የኢንዱስትሪ ምርቶች እንዲሁም የማዕድን ምርቶችም ለውጪ ገበያ እንደሚቀርቡ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ለአሐዱ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ