መስከረም 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ባወጣው የተሽከርካሪ ሰሌዳ ለውጥ መመሪያ መሠረት አዲሱ የተሸከርካሪ ሰሌዳ የመቀየር ሥራ ከሁለት ወራት በኋላ እንደሚጀመር በሚኒስቴሩ የትራንስፖርት አገልግሎት እና ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ አቶ አሰፋ ሀዲስ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
አማካሪው ከአሐዱ ሬዲዮ "ሁሉ ደህና" ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሰሌዳ አይነቶችና ምልክቶች መወሰኛ እና የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ 1050/2017 ሆኖ መጽደቁን አስታውሰዋል፡፡
ይህም አሰራር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትክክለኛ የሆነ የተሽከርካሪ ቁጥራዊ መረጃ ለማግኘት እና ለማወቅ እንደሚያስችለው ገልጸዋል።
የሰሌዳ ለውጥ መመሪያው ዋነኛ ዓላማም፤ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ታሳቢ ያደረገ ሰሌዳ በሀገሪቱ እንዲኖር ማስቻል እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
በሀገሪቱ ትክክለኛ የሆነ የተሽከርካሪዎች ቁጥራዊ መረጃ የማግኘት ችግር መኖሩን የገለጹት አቶ አሰፋ፤ ይህም ችግር እስካሁን መፍትሄ አለማግኘቱን ተናግረዋል፡፡
መረጃ አያያዙ በወረቀት መሆኑ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ አለመሆኑ ክፍተቱን እንደፈጠረው ገልጸው፤ አዲሱ የተሸከርካሪ ሰሌዳ የመቀየር ሥራ ይህንንም ሆነ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን እንደሚፈታ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ከዚህ በፊት የሰሌዳ አሰጣጥ አገልግሎት ላይ የነበሩ፤ የፎርጅድ እና መሰል ብልሹ አሰራሮችን እንዲሁም፤ የሰሌዳ አመራረት፣ አሰረጫጨትና የአወጋገድ ችግሮችን መመሪያው ይፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
ይህም የተሸከርካሪ ሰሌዳ የመቀየር ሥራ ከሁለት ወራት በኋላ እንደሚጀመር የገለጹት አማካሪው፤ በዚህም ከዚህ በፊት የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች የቀድሞውን ሠሌዳ በመመለስ አዲስ የተሸከርካሪ የመለያ ቁጥር ሠሌዳ እንዲወስዱ የማድረግ ሥራ ይሰራል ብለዋል።
በሌላ በኩል በዚህ ዓመት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ለሚሆኑ ተሽከርካሪዎች የጋዝ ልቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያ እንደሚገጠምላቸው፤ የትራንስፖርት አገልግሎት እና ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪው አቶ አሰፋ ሀዲስ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

70 በመቶ ወይም አብዛኛዎቹ ተሽከርካሪዎች በመዲናዋ የሚገኙ እንደመሆናቸው፤ መሳሪያውን የመግጠም ሥራው በአዲስ አበባ እንደሚጀመር አንስተዋል፡፡
የጋዝ ልቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያን የመግጠም ፍቃድ እና ቁጥጥርን በተመለከተ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሰራም ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
ይህም ሥራ በቀጣይ በክልሎች ተግባራዊ እንደሚሆን አንስተው፤ የአሰራር ስርዓቱ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የማረም እና የማስተካከል ሥራ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
በዚህ አሰራር በክልሎች የሚገጥም ችግርን ለመፍታት በክልል የተቋቋመው የትራንስፖርት ሴክተር ጉባኤ መኖሩን አንስተው፤ ፍቃድ የሚሰጡ ተቋማት ብቁ ካልሆኑ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሰሌዳ አይነቶችና ምልክቶች መወሰኛ እና የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ 1050/2017 መሠረት፤ አሁኑ በሥራ ላይ ያሉ የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች ላይ የሚቀመጠው የተለያዩ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች መለያዎች ተመሳሳይ መለያ እንዲኖራቸው ያስገድዳል።
በዚህም መሠረት በሀገሪቱ የሚመዘገቡ ሁሉም ተሸከርካሪዎች የሚለጥፉት የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ላይ፤ የኢትዮጵያ ካርታ እንዲሁም ኢትዮጵያ ባጸደቀችው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት የተሰጣትን ሀገራዊ ልዩ ምልክት "ETH" እና " ኢት" የሚል የግእዝ ፊደላት እና የላቲን ፊደላት ይዘት እንዲኖረው ይደረጋል ተብሏል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ