መስከረም 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ትምህርት ሚኒስቴር የ2017 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ውጤት ላይ ማሻሻያ ማድረጉን ተከትሎ፤ በአጠቃላይ 3,350 ተጨማሪ ተማሪዎች ዝቅተኛውን የማለፊያ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታውቋል፡፡

አገልግሎቱ ከ2017 የትምህርት ዘመን ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ጋር ተያይዞ በዛሬው ዕለት ማብራሪያ ሰጥቷል።

በማብራሪያውም የተፈታኞችን ውጤት የገለጸ ሲሆን፤ ተፈታኞች በተገለጸው ውጤታቸው እና ተያያዥ መረጃዎች ላይ ቅሬታቸውን በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማቅረባቸውን አስታውቋል፡፡

የቅሬታ አቅራቢዎች ብዛት በከፍተኛ ደረጃ ከዓመት ዓመት እየቀነሰ መምጣቱን የገለጸው አገልግሎቱ፤ "በ2017 ላይ በየይነ መረብ በተፈተኑ በተወሰኑ ተማሪዎች ላይ የፊዝክስ ውጤት ወደ መቶኛ ያልተቀየረላቸው እንዲሁም፤ ወደ መቶኛ ሲቀየር በነጥብ ቤት የነበሩ ቁጥሮች ያልተደመረላቸው ተማሪዎች ተስተካክሎላቸዋል" ብሏል፡፡

በተጨማሪም 49 ነጥብ 50 እና በላይ አማካይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ውጤታቸው ወደ 50 በመቶ እንዲጠጋጋ በተወሰነው መሠረት ተግባራዊ መደረጉን ገልጿል፡፡

በመሆኑም በአጠቃላይ 3 ሺሕ 350 ተጨማሪ ተማሪዎች ዝቅተኛውን የማለፊያ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን አስታውቋል፡፡

በዚሁ መሠረት የ2017 ትምህርት ዘመን ላይ 50 ከመቶና በላይ ያመጡ አጠቃላይ ተፈታኞች 52 ሺሕ 279 ሆነው የተመዘገቡ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በመቶኛ ሲገለጽ ወደ 8 ነጠብ 9 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን አገልግሎቱ ገልጿል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በዓመቱ በየትምህርት መስኩ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተፈታኞች ሥም ዝርዝርን ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም መሠረት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተፈጥሮ ሳይንስ በወንዶች ካሊድ በሽር 592 ነጥብ 08 ከ600 በማምጣት እንዲሁም፤ ሃይማኖት ዮናስ 581 ነጥብ 36 ከ600 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸው ተገልጿል፡፡

እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስ በወንዶች ጫላ ግርማ 563 ነጥብ 50 ከ600 እንዲሁም በሴቶች ሲምቦ ደረጄ 549 ነጥብ 78 ከ600 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡

👉 በዓመቱ በየትምህርት መስኩ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተፈታኞች ስም ዝርዝር ከሥር ተያይዟል

Post image


#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ