መስከረም 30/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) መስከረም 21 ቀን 2018 ዓ.ም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ማርያም ቤተክርስቲያን በደረሰው አደጋ ምክንያት ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው አብዛኞቹ ሰዎች በአዲስ አበባ በሚገኙ የሕክምና ተቋማት ውስጥ ክትትል እያደረጉ እንደሚገኝ የአረርቲ ከተማ አስተዳደር ለአሐዱ አስታውቋል።

በደረሰው አደጋ ከ30 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን ያነሱት የከተማው ከንቲባ አቶ ተሻለ ጥላሁን፤ 22 የሚሆኑት በሆስፒታል ደረጃ ተመርምረው ሕይወታቸው ማለፉ ተረጋግጦ ከሆስፒታል የወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች ደግሞ ከአደጋ ቦታው ሕይወታቸው እንዳለፈ ሲታወቅ ቤተሰቦች ወደተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች ይዘዋቸው ሂደው ስርአተ ቀብራቸው የተፈፀመ እንዲሁም፤ ወደ አዲስ አበባ የሄዱም መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በእርግጠኝነት በአደጋው ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎችን ቁጥር መግለጽ እንደማይቻል ገልጸው፤ ነገር ግን አጠቃላይ ከ30 ያላነሰ የሰው ሕይወት መጥፋቱን ተናግረዋል።

በከፍተኛ ደረጃ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውና በርካታ ገንዘብ ለሕክምና የተጠየቁ 6 የሚያክሉ ታካሚዎች ናቸው ያሉት ከንቲባው፤ ለሕክምና ውጪያቸውም በየግላቸው ከ800 ሺሕ እስከ 1 ሚሊዮን ብር ድረስ መጠየቃቸውን ገልፀዋል።

ይህንን በማስመልከትም ለተጎጂዎች እርዳታ ለማሰባሰብ ማህበረሰቡ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት የእርዳታ ገንዘብ አሰባሳቢ እና ተጎጂዎች ምን አይነት ደረጃ እንደሚገኙና ምን ያክል ወጪ እየተጠየቁ እንደሚገኝ የሚከታተል የሕክምና ክትትል ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ 70 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው አረርቲ ማርያም ቤተክርስቲያን ለግንባታ የተረበረበ እንጨት ተደርምሶ፤ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ የታደሙ የበርካታ ምዕመናን ሕይወት ሲያልፍ ከ200 በላይ ሰዎች ከባድ እና ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወሳል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ