ሕዳር 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የሐዋሳ ከተማ ም/ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ አቶ ጥራቱ በየነን የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አድርጎ ሾሟል።

አቶ ጥራቱ በየነ ከዚህ ቀደም ከነሐሴ 24 ቀን 2011 ዓ.ም እስከ 2013 ዓ.ም የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሆነው የመሩ ሲሆን፤ ላለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማው ከፍተኛ አመራር ሆነው አገልግለዋል።
በዛሬው ዕለትም የሐዋሳ ከተማ ምክር ቤት በጠራው 2ኛ ዙር 10ኛ ሥራ ዘመን 2ኛ አሰቸኳይ ጉባኤ አቶ ጥራቱ በየነን የከተማዋ ከንቲባ እንዲሆኑ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

አቶ ጥራቱ ያካበቱትን የረጅም ጊዜ እውቀትና ልምድ በመጠቀም የከተማዋን ሁለንተናዊ ለውጥና እድገት ለማረጋገጥ ከህብረተሰቡ ጋር በጠንካራ ትስስር ለመሥራት ቃል ገብተዋል።
በቅርቡ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ሆነው ተሹመው የነበሩት አቶ ተክሌ ጆንባ፤ የፌደራል እንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንዲሰሩ መመደባቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ