ሕዳር 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሸገር ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ከ3 ሺሕ በላይ ታራሚዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ከልጆቻቸው ጋር የሚኖሩ እና እዛው የሚወልዱ ወላጆች መኖራቸውን የከተማ አስተዳደሩ የማረሚያ ቤቶች ጥበቃ እና ደህንነት ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር በላይ ፈይሳ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
ሕጻናቱ ወንጀል ባይኖርባቸውም ከወላጆቻቸው መለየት ስለማይችሉ ብቻ አብረው እንዲኖሩ ይደረጋል ያሉት ኃላፊው፤ በፖሊስ እጀባ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
ከመዋለ ሕጻናት ጀምሮ ትምህርቱ እንደሚሰጥ የገለጹም ሲሆን፤ የአጋር አካላት ትብብር እንደሚያስፍልግም ጠቁመዋል፡፡
ልጆች ብቻም ሳይሆን አዋቂዎችም እራሳቸው መደበኛ ትምህርት እንዲማሩ፣ ሸማ ሥራ፣ ልብስ ስፌት፣ የእርሻ ስራ የመሳሰሉትን በመስራት እራሳቸው በእውቀት እና ክህሎት እንዲያሳድጉ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ 'ከወላጆቻቸው ጋር በማረሚያ ቤት የሚኖሩ ሕጻናት ለምን ያክል ጊዜ አብረው መቆት ይችላሉ?' የሚለውን የሚደነግግ ሕግ ቢኖርም፤ አብዛኞቹ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚገቡ ወላጆች ሕጻናቱን ተቀብሎ የሚያሳድግላቸው በማጣታቸው ልጆቹ አድገውም ከወላጆቻቸው ጋር በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚቆዩበት ሁኔታ መኖሩን አሐዱ ከዚህ ቀደም መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ማረሚያ ቤት ያሉ ሕጻናት በፖሊስ እጀባ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እንደሚደረግ ተገለጸ