ሕዳር 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፤ መንግሥት የማያውቃቸውና ለምርቶች ነፃ ዝውውር ተግዳሮት የፈጠሩ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ሕገ-ወጥ ኬላዎችን ማንሳት መጀመሩን አስታውቋል።
ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ እና በየትኛዎቹ ክልሎች እንደሚገኙ ያልተገለጸውን "ሕገ-ወጥ" የተባሉ ኬላዎች ከአገልግሎት ውጭ ለማድረግ፤ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ተብሏል።

"የሕገ-ወጥ ኬላዎች መብዛት ምቹ የንግድ እንቅስቃሴን አውኳል" ያሉት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ፤ የኬላዎቹ መፍረስ የምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ መቅረብና ያለ ገደብ መሰራጨት ያረጋግጣል፣ ሆነ ተብሎ የሚፈጠርን የምርት እጥረት ይከላከላል፣ ለውጭ ገበያ የሚበርቡበትን እድል ያሰፋል" ብለዋል።
የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አያይዘውም በ2017 በጀት ዓመት ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ይህም ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ እንደነበር ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 9 ነጥብ 4 ቢልዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ውስጥ ባለፉት ሦስት ወራት 2 ነጥብ 48 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ጠቁመዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ከ297 በላይ ሕገ-ወጥ ኬላዎች መኖራቸውን በመግለጽ፤ ኬላዎቹ ለማፍረስ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ቢሆንም፤ በዚህ ሕገ-ወጥ ተግባር ላይ የፀጥታ አካላትም በስፋት የሚሳተፍበት በመሆኑ ችግሩ አሁንም ድረስ መዝለቁን ስለማስታወቁ አሐዱ ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ