ሕዳር 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ እና የጨፌ ኦሮሚያ አባል አቶ ታዬ ደንደአ በዛሬው ዕለት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግሥት እና በሕገ መንግሥት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት ቀርበዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት የቀረቡበት ምክንያት ከዚህ ቀደም ጥፋተኛ በተባሉበት እና ችሎቱን የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት በሰማበት "የፀና ፍቃድ ሳይኖር የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት" ወንጀል ቅጣት ለመስማት ዐቃቤ ሕግ ሕዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም ባቀረበባቸው ሦስት ተደራራቢ ክሶች የተከሳሽ የክስ መቃወሚዎች በክስ ለማቅረብ እና ዋስትና የሚመለከት ክርክር ለመስማት ነበር።

ለዛሬ በተቀጠረው የቅጣት ውሳኔ መሰረት ችሎቱ በአቶ ታዬ በኩል የቀረቡትን የቅጣት አስተያየቶች በተለይም የጤናቸው ምክንያት በማስረጃ የቀረበበት ባለመሆኑ፤ ውሳኔው ከመሰማቱ በፊት የቅጣት ማቅለያዎችን እንዲያቀርቡ እና የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለሕዳር 26 ቀን 2018 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን ጠበቃቸው አበራ ንጉሥ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋ።

በዛሬ ውሎ አቶ ታዬ ደንደአ በጠበቃቸው በኩል የ"ዋስትና መብት ይፈቀድልኝ" ጥያቄ በችሎቱ በማቅረባቸው ምክንያት ዋስትናን በተመለከተ ሰፊ የሕግ እና የፍሬ ነገር ክርክር አድርገዋል።

በዚህም በጠበቃቸው በኩል ያቀረቧቸውን የክስ መቃወሚያዎች ችሎቱ ተቀብሎ ለዐቃቤ ሕግ እንዲደርሰው በማድረግ በቀረቡት የክስ መቃወሚያዎች ላይ አስተያየታቸውን በፅሑፍ እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ለታሕሳስ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡

Post image

በአቶ ታዬ በኩል የወንጀል ሥነ-ስርዓትና የሰበር ውሳኔዎች በዋቢነት በመጥቀስ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው በመከራከሪያነት ያቀረቡ ሲሆን፤ ዐቃቤ ሕግም የዋስትና መብት ጥያቄያቸውን ውድቅ እንዲሆን በመቃወም ክርክር ያደረጉ መሆኑን ጠበቃው አብራርተዋል።

ዐቃቤ ሕግ በመከራከሪያነት ያቀረበው ብቸኛ ምክንያት "አቶ ታዬ ደንደአ በ'ሆርን ኮንቨርሴሽን' ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ተከትሎ ንግግራቸው ከፍተኛ የሕዝብ ተቀባይነት ያገኘ በመሆኑ፤ ይህም በዋስ ቢወጡ ይህንን ሕዝባዊ ተቀባይነት በመጠቀም ወይም ድጋሚ በመቀስቀስ መንግሥት በሕዝባዊ ዓመፅ ለመጣል ሊንቀሳቀሱ ስለሚችሉ በእስር ሆኖው መከራከር አለባቸው" የሚል መሆኑንም ጠበቃው ገልጸዋል።

በዚህም የክርክር ሂደት በሆርን ኮንቨርሴሽን ያደረጉትን ንግግር ተቀባይነት ማግኘቱን ለችሎቱ ግልፅ ለማድረግ በሚል ሀሳብ፤ በእያንዳንዱ ቪዲዮዎች የተሰጡ አንድ ሺሕ የሚሆኑ የተመልካቶች አስተያየቶች መመልከቱን ለችሎቱ አስታውቋል

ግራ ቀኙን የሰማው ችሎቱ 'ዋስትና ይፈቀድላቸው' ወይንስ 'አይፈቀድላቸው' የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ፤ ለታህሳስ 8 ቀን 2018 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃ አበራ ንጉሥ ለአሐዱ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ