ሕዳር 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት የሚፈጸሙ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ለሥነ-ልቦናዊ ጫና እያደረጋቸው እንደሚገኝና፤ አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አፍላ ወጣት ሴቶች ለአሐዱ ሬዲዮ አቤቱታዎችን አሰምተዋል።
እንደ ቅሬታ አቅራቢዎች ገለጻ፤ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች ለድብርት እና ለሌሎች ሥነ-ልቦናዊ ጫና እያጋለጣቸው ይገኛል። ከዚህም አለፍ ሲል ዛቻና ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸው ጠቅሰዋል።
አብዛኛዎቹ ጥቃቶች የሚፈጸሙት በሰላማዊ ጊዜ ልውውጥ ያደረጓቸውን ተንቀሳቃሽ ምስል እና ፎቶን በመያዣነት በመጠቀም እንደሆነ ገልጸዋል።
ጥቃቶች በዋናነት በማታለል አማካኝነት እንደሚፈፀሙ የተናገሩም ሲሆን፤ አለፍ ሲል ሁኔታዎች ከተለመደው ወጣ ብለው እንደሚፈጸሙ አስታውቀዋል።
አክለውም በጥቃቱ ሰለባ ከሆኑ በኋላ ወደየት በመሄድ መፍትሔ ማግኘት እንደሚቻል እንደማያውቁ አሳስበዋል።
አፍላ ወጣቶች፣ እናቶች ላይ የግል መረጃን በፎቶ እና በተንቀሳቃሽ ምስል በመቅረፅ፤ 'በማህበራዊ ሚዲያ እለቀዋለሁ' በሚል ዛቻና ማስፈራሪያ ከቤተሰቦቻቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ንብረት የሚሰበስቡ ግለሰቦች መኖራቸውን አሐዱ ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል።
ይህንን ወንጀል የሚፈፅሙ ግለሰቦች ኑሯቸውን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ማድረጋቸውንና በዚህ ወንጀል በርካቶች ሀብት ንብረታቸውን እያጡ እንደሚገኙ አቤቱታዎችን ሲያሰሙ ይደመጣል።
አሐዱም ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ ፍትሕ ሚኒስቴርን አነጋግሯል።
በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የሚፈጸሙ ጥቃቶች ታዳጊዎችን ለከባድ ችግር እንደሚጋልጣቸውና ከዚህም በተጨማሪ ሕይወታቸውን እንዲያጡ እንደሚያደርግ ለአሐዱ የተናገሩት፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶች እና ሕጻናት ዴስክ ዳይሬክተር ዳግማዊት ተረፈ ናቸው።
አብዛኛው በግንዛቤ እጥረት የተነሳ ለጥቃቱ ሰለባ እንደሚሆኑ በመግለጽም፤ በጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሕጻናት የሥነ-ልቦና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።
በአካል ከሚደረጉ የአስገድዶ መደፍር ጥቃት ባልተናነሰ መልኩ በማሕበራዊ ሚዲያዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች ጉዳት እንደሚያደርስባቸው አስታውሰዋል።
በተጨማሪም ሕይወታቸው ላይ አላስፈላጊ ነገሮችን ተፈጻሚ እንዲያደርጉ እንደሚጋብዛቸውም ጠቁመዋል።
ችግሩን ለመከላከል በተለያዩ መንገዶች ግንዛቤ ማስጨበጥ እንዲሁም የጥቃት ሰለባ የሆኑ ወላጆችን እንዴት መከታተል መቆጣጠር እንደሚችሉ ማስገንዘብ ይጠበቅብናል ብለዋል።
ድርጊት ፈጻሚዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሰፊ ምርመራ እንደሚጠይቅ ነግረውናል። የሕግ ሽፋኑን በተመለከተ አሁን ጉዳዩ በኮምፒውተር አዋጅ እንደሚታይ አስታውሰው፤ "ይህ አዋጅ የሚሻሻልበት ሁኔታ የሚታይ ይሆናል" ሲሉ አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የሚፈጸምብን ጾታዊ ጥቃት ሥነ-ልቦናዊ ጫና እያሳደረብን ነው ሲሉ ወጣት ሴቶች ገለጹ
ፍትሕ ሚኒስቴር በበኩሉ 'በማህበራዊ ሚዲያ የሚፈጸሙ ጥቃቶች አሳሳቢ ጉዳይ ሆነዋል' ሲል አስታውቋል