የማይፈጸሙ የፍርድ ቤት ትዕዛዞች እና የሚያሳድሩት ጫና
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 6 በግልጽ እንደሚያስቀምጠው በሕግ ቁጥጥር ሥር ያሉ ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብታቸው ይጠበቅላቸዋል።
ኢትዮጵያ ፈርማ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችም የተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት መከበር እንዳለበት የሚታገሉ ናቸው።
ይህ ሁሉ ቢሆንም፤ ፍርድ ቤቶች በእስር ላይ ላሉ ተጠርጣሪዎች የሚሰጧቸው የዋስትና መብት የሚፈቅዱ ትዕዛዞች ሳይፈጸሙ፣ ሲጓተቱ እና ሲጣሱ ይስተዋላል።
ይህ ዓይነቱ የሕግ ጥሰት የግለሰቦችን ከፍርድ በፊት እንደ ነጻ የመታየት መብት ብቻ ሳይሆን የፍትሕ ሥርዓቱ ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚከት ተደጋግሞ ተነስቷል።
ይህንን መሰል የፍርድ ቤትን ስልጣን የሚጋፋ ድርጊት በርካቶች ሲቃወሙት፤ እንዲስተካከል ሲታገሉለት ቢቆዩም ተፅዕኖ እንደሚያሳድር በመግለጽ የፍትሕ አካላት የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ ሲጠየቅ ቆይቷል።
በተለይም የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ባለመፈጸም ግለሰቦችን ከሕግ ውጪ በእስር የሚያቆዩ የፖሊስ አባላትና ኃላፊዎች ላይ ተገቢው ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ በተደጋጋሚ ጥያቄ ይቀርባል።

ይህ ችግር በክልልና በፌዴራል ደረጃ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡ የተለያዩ ትዕዛዞች ሳይፈጸሙ የሚቀሩበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ሲታይ ቆይቷል። በቅርቡ የዓለም ፕሬስ ነፃነት ጀግና ተሸላሚ የሆነውን ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስን ጉዳይ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። የዋስትና መብቱ በፍርድ ቤት ቢረጋገጥም፣ የፍርድቤቱ ትእዛዝ የተፈጸመው ከቀናት በኋላ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በተመሳሳይ ሌሎች ሁለት ሴት ጋዜጠኞች ላይ የተፈጠረው የፍርድ ቤትን የዋስትና መብት አለማክበርም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ የዚህን መሰል ችግሮች በአብዛኛው ተጠርጣሪ ላይ የሚያጋጥሙ ቢሆንም ከጋዜጠኞች በተጨማሪ በፖለቲከኞች እና በአክቲቪስቶች ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጸም ይስተዋላል።
ባለፈው ዓመት በተቀሰቀሰው የጤና ባለሙያዎች የሥራ ማቆም አድማ ወቅት በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል በባሕር ዳር ከተማ በሚገኙ የአዲስ ዓለምና የፈለገ ሕይወት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ይሰሩ የነበሩ 6 የጤና ባለሙያዎች ይገኙበታል።
እነዚህ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው በዋስትና እንዲፈቱ ቢወሰንላቸውም፣ ፖሊስ ውሳኔውን አክብሮ በተባለው ጊዜ ሳይለቃቸው መቆየቱ ይታወሳል። ይህ ዓይነቱ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያለመፈጸም የሕግ ሂደቱን ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል።
"ይህንን ድርጊት ፍርድ ቤቶች ለምን ማስቆም አልቻሉም?" ይህንን ጥያቄ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ፉአድ ኪያር አቅርበን ነበር። ፕሬዚዳንቱ በአፈጻጸም ላይ ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውን ይናገራሉ።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም ፍርዶችን በውይይትና በመነጋገር ለማስፈጸም ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል። ከአፈጻጸም አንጻር ግልጽ የሆኑ ችግሮች መኖራቸውን የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ዳኞች ፍርዱን እንዲያስፈጽሙ ለማድረግም እንደሚሠራ አብራርተዋል።
በተደጋጋሚ ጊዜ በፍርድ ቤት በነፃ የተሰናበቱም ሆኑ በዋስትና እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት የወሰነላቸው ዜጎች ተጨማሪ ቀን በፖሊስ ጣቢያ ሲያሳልፉ ይስተዋላል። በርካታ ሰዎች ይህን ሁኔታ የሕግ የበላይነትን አለመከበር መሆኑን ያነሳሉ።
ታዲያ "ይህንን ችግር ከመስቆምና መፍትሔ ከመስጠት አኳያ ፍርድ ቤቶች ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ወይ?" ስንል በድጋሚ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ፉአድ ኪያርን ጠይቀን ነበር።
ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎችን ለማስፈጸም እየሠሩ መሆኑንና ውሳኔውን በተዋረድ በጠበቀ መንገድ ለማስፈጸም እንደሚሠራ ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ፣ አካልን ነፃ የማውጣት (Habeas Corpus) የተባለ ችሎት ማቋቋማቸውን ገልጸዋል።
ወንጀልን የመከላከልና ወንጀል ፈጻሚዎችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ የፖሊስ፣ የዐቃቤ ሕግ፣ የፍርድ ቤቶችና የማረሚያ ቤቶች የተቀናጀ ኃላፊነት ነው።
ፖሊስ የወንጀል መከላከልና ተጠርጣሪዎችን ለሕግ የማቅረብ ኃላፊነት አለበት። ፍርድ ቤት ደግሞ በቀረበው ማስረጃ መሠረት ውሳኔ ይሰጣል። በመሆኑም፣ ይህንን የፍርድ ቤት ውሳኔ ማክበርና መፈጸም የፖሊስ ኃላፊነት ቢሆንም፣ ክፍተቶች ይስተዋሉበታል።
አቶ ፉአድ ኪያር ፖሊስም፣ ዐቃቤ ሕግም ሆነ ፍርድ ቤት ውሳኔዎችን የሚያከብሩት የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ስለሚገባቸው መሆኑን ይናገራሉ።
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የዳኝነት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዳኛ ዳንኤል አበበ በበኩላቸው፣ ፖሊስ ጊዜ ቀጠሮ ላይ "ሌላ ወንጀል ጠርጥሬያለሁ" ወይም "ይግባኝ ልጠይቅ እችላለሁ" ሊል እንደሚችል ገልጸዋል።

ነገር ግን ፍርድ ቤቱ እንዲለቀቅ ከወሰነ፤ ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አክብሮ መፈጸም እንደሚገባው አፅንዖት ሰጥተዋል።
ዜጎች የተፈረደላቸውን ፍርድ በአጭር ጊዜ የማግኘት መብት በሕገ-መንግሥቱ የተሰጠ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ መንግሥቱ አበባው፤ የፍርድ ቤት ውሳኔን የማይፈጽሙ የፖሊስ አካላትን የማስጠየቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት መቋቋሙ ይህንን ችግር ይቀርፋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ክስ ሲመሠርት፣ ፍርድ ቤት በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት ማስረጃዎችን ተመልክቶ ውሳኔ ይሰጣል። ፍርድ ቤት አንድን ተጠርጣሪ ይለቀቅ ካለ መልቀቅ ያለበት ፖሊስ ነው። ሆኖም ዐቃቤ ሕግ የበላይ ተቆጣጣሪ እንደመሆኑ፣ ፖሊስ ያለፈቃድ ሰዎችን ይዞ ካስቀመጠ "ልቀቅ" ብሎ የማዘዝ ሥልጣን እንዳለው ይገለጻል።
ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ እንዲታሰሩ አልፈቅድም ብሎ መዝገቡን ከዘጋ በኋላ ፖሊስም አልለቅም ካለ፣ በአቃቤ ሕግም ሆነ በበላይ ፖሊሶች መፍትሔ ካልተገኘ በፍትሐብሔር መጠየቅ እንደሚቻልም ይነሳል።

በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ፣ በሕገ መንግሥቱና በዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተረጋገጠው የዜጎች የዋስትና መብት በፍርድ ቤት ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በአፈጻጸም ችግር ምክንያት እየተጓተተ መሆኑ የሕግ የበላይነትን የሚፈታተን አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ የፍትሕ አካላት ኃላፊዎች የአፈጻጸም ክፍተቶች መኖራቸውን ቢቀበሉም፣ ይህንን የቆየ ችግር ለመፍታት በውይይት፣ አካልን ነፃ የማውጣት ችሎት በማቋቋም እና የፖሊስ አካላትን በማስጠየቅ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ይሁን እንጂ፤ የፍርድ ቤት ውሳኔን ባለማክበር ዜጎችን ከሕግ ውጪ በእስር የሚያቆዩ የፖሊስ አባላት ላይ የሚወሰደው ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ተጠናክሮ ካልቀጠለና የዐቃቤ ሕግ የቁጥጥር ሥልጣን በአግባቡ ካልተተገበረ፣ የዋስትና መብት ጥበቃው እውን ሊሆን አይችልም።
የዜጎች የፍትሕ የማግኘት መብት እንዲረጋገጥ፣ በፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ ያለምንም ማመንታትና መጓተት መፈጸም አለበት። ይህ ደግሞ በሁሉም የፍትሕ አካላት ማለትም በፖሊስ፣ በዐቃቤ ሕግና በፍርድ ቤት መካከል ያለውን የተቀናጀ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ይጠይቃል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ