ሐምሌ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሰላም ሽልማት እጩነት እንዲበቁ ለኖቤል ኮሚቴ የላኩትን ደብዳቤ ትናንት ማምሻውን ለፕሬዝዳንቱ አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ትናንት ምሽት ላይ በዋይት ሀውስ የእራት ግብዣ አድርገውላቸዋል።

በዚህም በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እና ከኢራን ጋር የሚደረገውን ድርድር ለመወሰን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁለቱ መሪዎች ያላቸውን ሚና እያነሱ እርስ በእርስ ተወዳድሰዋል፡፡

በዚህም ወቅት "የሁሉም እስራኤላውያንን ብቻ ሳይሆን የአይሁድን ሕዝብ ምስጋና እና አድናቆት መግለጽ እፈልጋለሁ" ብለዋል ኔታንያሁ ለትራምፕ ያላቸውን አድናቆት ሲገልጹ።

በመቀጠልም ፕሬዝዳንቱን ለኖቤል የሰላም ሽልማት እጩ አድርገው የፃፉትን ደብዳቤ ለትራምፕ ያቀረቡ ሲሆን፤ ትራምፕ ደብዳቤውን በሚያነቡበት ወቅት ኔታንያሁ "እርሶን ለሰላም ኖቤል ሽልማት በእጩነት ያቀረበ ነው። ሽልማቱ ይገባዎታል፤ ሊያገኙትም ይገባል" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው "በተለይ ይህ ከእርስዎ መምጣቱ በጣም ትርጉም ያለው ነው" ብለዋል።

አክለውም ሀገራቸው ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት ላይ የመከላከል አቅሟን ለማገዝ ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ዩክሬን ለመላክ ቃል ገብተዋል።

"ተጨማሪ የጦር መሣሪያዎችን እንልካለን፡፡ መላክም አለብን" ያሉት ትራምፕ "ዩክሬናዊያን እራሳቸውን መከላከል መቻል አለባቸው። አሁን በጣም እየተመቱ ነው። ስለሆነም ተጨማሪ መሳሪያ መላክ አለብን።" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በቅርቡም ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ ያደረጉትን ውይይት አስመልክቶ "በጣም ተበሳጭቻለሁ" ሲሉ ገልጸው፤ ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ትራምፕ እና ኔታንያሁ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሁለቱም መሪዎች የአጭር ጊዜ ስምምነቶችን አስፈላጊነት ላይ አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን የረጅም ጊዜ መፍትሄዎችን በተመለከተ ልዩነቶች አሁንም ግልጽ እንደሚታዩ የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ አመላክቷል።

ትራምፕ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል፤ ከኢራን ጋር ተጨማሪ ውይይቶችን ለማድረግ ቀጠሮዎች መያዛቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በረዳቶቻቸው በኩል በሚቀጥለው ሳምንት ወይም ከሳምንት በኋላ ውይይቱ እንዲቀጥል እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

ኔታንያሁ ግን አሁንም ውጥረቱ እንደቀጠለ ጠቁመዋል።

ኔታንያሁ "አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ያደረሱት ጥቃት ታሪካዊ ድል አስመዝግቧል" ያሉ ሲሆን "ዛሬ እዚህ ተቀምጠን ውይይት በምናደርግበት ወቅት ይህ እርምጃ ቀድሞውኑ የመካከለኛው ምስራቅን ገፅታ ቀይሯል" ብለዋል፡፡ አክለውም "እናም ተስፋ አደርጋለሁ ኢራን ጥንካሬያችንን አይፈትንም፡፡ ምክንያቱም ስህተት ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ትራምፕ በበኩላቸው በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ "እነሱ መገናኘት ይፈልጋሉ እናም የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ ይፈልጋሉ። ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኔታንያሁ በበኩላቸው፤ "እኔ እንደማስበው ፍልስጤማውያን እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ስልጣን ሊኖራቸው ይገባል ነገር ግን እኛን የሚያስፈራሩን የትኛውም ኃይላት የሉም” ያሉ ሲሆን፤ "ይህ ማለት እንደ አጠቃላይ ደህንነት ያሉ አንዳንድ ኃይሎች ሁል ጊዜ በእጃችን ይቆያሉ ማለት ነው" ሲሉም አክለዋል፡፡

"እኛ ሊያጠፉን ከማይፈልጉ ከፍልስጤማዊያን ጎረቤቶቻችን ጋር ለሰላም እንሰራለን፡፡ የደህንነት ሉዓላዊ ኃይሉ ሁልጊዜ በእጃችን የሚቆይበትን ሁኔታ በማስጠበቅም ለሰላም እንሰራለን" ብለዋል፡፡

ኔታንያሁ ከትራምፕ ጋር ያደረጉትን ውይይት አጠናቀው ከሰአት በኋላ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ እና የታቀደው የተኩስ አቁም ስምምነት አደራዳሪ ከሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

የዋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት 'ዊትኮፍ በዚህ ሳምንት ድርድሩን ለመቀጠል ወደ ዶሃ ለመጓዝ ማቀዳቸውን' ገልፀው፤ ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነት በዚህ ሳምንት ሊጠናቀቅ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ኔታንያሁ ከኮንግረስ አባላት፣ ከፔንታጎን ባለስልጣናት እና ከምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጋር ለመገናኘት ለሳምንት ያህል በዋሽንግተን ለመቆየት ማቀዳቸውም ተመላክቷል።

ይህ የኔታንያሁ የዋይት ሀውስ ጉብኝት ትራምፕ ስልጣን ከያዙ በስድስት ወራት ወራት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የተደረገ ነው፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ