ጥቅምት 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ዩክሬንን ከሩሲያ ጋር በሚደረገው ጦርነት የምትጠቀምባቸውን የረጅም ርቀት ቶማሃውክ ክሩዝ ሚሳኤሎች አሁን ላይ የማቅረብ ዕቅድ እንደሌላቸው አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እሁድ ዕለት በ"ኤር ፎርስ ዋን" ላይ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ የዩክሬኑ አቻቸው ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የጠየቁትን ሚሳኤል የመስጠት ስምምነት "አሁን ላይ አይሆንም፤ በእርግጥም አሁን አይደለም" በማለት ውድቅ አድርገዋል።

Post image

ሆኖም ግን አቋማቸውን ሊለውጡ እንደሚችሉ እድል እንደሚኖር አመልክተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ሚሳኤሎቹን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑበት ዋና ምክንያት፤ ጦርነቱ ይበልጥ እንዳይባባስ ለማድረግ በማሰብ እንደሆነ በመግለጽ ነው።

ትራምፕ፣ ሦስት ዓመት ያለፈው ይህ ግጭት ለሁለቱም ሀገራት "አስቸጋሪ ጦርነት" እንደሆነ ገልጸው፤ "አንዳንዴም እንዲዋጉት መተው አለብህ" በማለት ግጭቱን ሀገራቱ ራሳቸው የሚፈቱበት ጊዜው አሁን እንደሆነ ተናግረዋል።

የረጅም ርቀት ቶማሃውክ ክሩዝ ሚሳኤሎች እስከ 2 ሺሕ 500 ኪሎ ሜትር (1 ሺሕ 550 ማይል) የሚደርስ የጥቃት ርቀት ያላቸው ሲሆን፣ ዩክሬን ከተሰጣት ሞስኮን ጨምሮ በሩሲያ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ቁልፍ ኢላማዎችን ለመምታት የሚያስችል አቅም ይኖራታል።

ሚሳኤሉ ከመሬት ከ50 ሜትር እስከ 100 ሜትር ከፍታ ድረስ ዝቅ ብሎ መብረር የሚችል ሲሆን፤ ለአየር መከላከያ ሥርዓቶች ቁጥጥር አስቸጋሪ መሆኑም ተነግሯል።

Post image

ኪየቭ እነዚህ የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎች ፕሬዝዳንት ፑቲንን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ያመጣሉ ብላ ታምናለች።

ሩሲያ በበኩሏ፤ ቶማሃውክ ሚሳኤሎች ለዩክሬን መሰጠቱ ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያበላሽ እና ግጭቱን ወደ "አዲስ የማባባስ ደረጃ" እንደሚያሸጋግረው በተደጋጋሚ አስጠንቅቃለች።

ፕሬዝዳንት ፑቲን፤ ሩሲያ ለቶማሃውክ ጥቃት የምትሰጠው ምላሽ "እጅግ ጠንካራ፣ ምናልባትም ከዚያም በላይ አውዳሚ" ይሆናል ብለዋል።

ትራምፕ ከኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩት ጋር ከሳምንት በፊት በተገናኙበት ወቅት፤ አሜሪካ ሚሳኤሎቹን ለኔቶ አባላት በመሸጥ እነሱ ደግሞ ለዩክሬን እንዲያስተላልፉ ስለሚፈቅድ እቅድ ላይ መወያየታቸው ቢዘገብም፣ ፕሬዝዳንቱ ለአሁኑ እቅዱን አልተቀበሉትም ተብሏል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ