ጥቅምት 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የውጪ እርዳታ ማቋረጡን ተከትሎ፤ በኢትዮጵያ ከሥራ የተሰናበቱ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅት ሠራተኞችን ብዛት ለማወቅ የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
የእርዳታውን መቋረጥ ተከትሎ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ማኅበራት የተለያዩ አካባቢዎች ሲያካሂዱት የነበረውን እንቅስቃሴ ለማቋረጥ በመገደዳቸው፤ ከሥራ ውጭ የሆኑ ሠራተኞችን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ የተደረገው ጥረት በተቋማቱ ፈቃደኛ አለመሆን መስተጓጎሉን ነው ምክር ቤቱ የገለጸው፡፡
የምክር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ሁሴን፤ ከሥራ የተሰናበቱ ሠራተኞችን ትክክለኛ ብዛት ለማወቅ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ባለሥልጣን እና የሲቪል ማኅበረሰብ ምክር ቤት በጋራ ያሰናዱትን መጠይቅ ሞልተው ለመመስ አብዛኞቹ ተቋማት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም "ካሉት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ ፈቃደኛ ሆነው መጠይቁን የሞሉት ቁጥር ከ100 አይበልጥም" ብለዋል፡፡
አክለውም ተቋማቱ የገንዘብ ድጋፉ መቋረጥ ምክንያት የገጠማቸውን ችግር ለመቋቋም፤ ሠራተኞችን ከማሰናበት በተጨማሪ ወርሃዊ ደመወዝ ለመቀነስ እና ጥቅማ ጥቅም ለማስቀረት ተገደዋል ብለዋል።
በድጋፉ መቋረጥ ምክንያት ምን ያህል ሠራተኞች ከሥራ ውጭ እንደሆኑ ባይታወቅም፤ ሙሉ በሙሉ ከሥራ ውጭ የሆነ የሲቪል ማኅበር ግን የለም ተብሏል፡፡
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጥር 12 ቀን 2017 ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሠረት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ) የገንዘብ ዕርዳታ በድንገት መቆሙ፤ በበርካታ በድርጅቱ ድጋፍ በሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ሥራ እና የሰብዓዊ እና የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ ይታወቃል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ መቋረጥ ምክንያት ከሥራ የተሰናበቱ ሠራተኞችን ብዛት ለማወቅ የተደረገው ጥረት አለመሳካቱ ተገለጸ
ከ5 ሺሕ በላይ ሲቪል ማኅበራት ቢኖሩም፤ መጠይቁን የሞሉት ከ100 አይበልጡም ተብሏል