ሕዳር 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) አዶት ሲኒማ እና ቲያትር የተመልካች መግቢያ ትኬት በዲጂታል መተግበሪያ ለመቀበል የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከእናት ባንክ እና ከመልቲ የትያትር ቡድን ጋር ተፈራርሟል።
ይህ አሰራር ተመልካቾች ትኬቶችን በእናት ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ሲስተም አማካኝነት መቁረጥ የሚያስችላቸው ይሆናል ተብሏል።
ይህ የዲጂታል ትኬት ሽያጭ ሥርዓት "መልቲ" ለተሰኘው ኮሜዲ ትያትር ተመልካቾችን በሚመለከት የተፈረመ ቢሆንም፤ በቀጣይ በሌሎች ትያትር እና ሲኒማ ቤቶችም ተፈጻሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

"መልቲ" የተሰኘው የኮሜዲ ዘውግ ያለው ትያትር መልቲ በተሰኘ የትያትር ቡድን የተዘጋጀ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ማዘጋጃ ቤት ለዕይታ ቀርቦ በተመልካቾች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትና ተወዳጅነትን አግኝቶ እንደነበር በዛሬው ዕለት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተነግሯል።
ከትያትሩ ተዋንያን መካከል ምትኩ በቀለ፣ ኤልሻዳይ ከበደ፣ ሱራፌል ብስራት፣ ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው፣ አቤል ሰለሞን፣ ሰላማዊት ካሳዬ ይገኙበታ፡፡
በኮሜዲ ዘውግ የተዘጋጀው እና ታሪኩን በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሕይወት ላይ ያደረገው "መልቲ" የተሰኘው ትያትር ሕዳር 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ታላላቅ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ መምህራን እና የተመረጡ እንግዶች በተገኙበት በቀይ ምንጣፍ ሥነ-ስርዓት እንደሚመረቅ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።

ከምርቃቱ በኋላም ትያትሩ ዘወትር አርብ በ12፡00 ሰዓት ብስራተ ገብርኤል በሚገኘው አዶት ሲኒማ መታየት ሲጀምር፤ ተመልካቾች የመግቢያ ትኬቱን በአዲሱ የዲጂታል ስርዓት አማካኝነት ያገኛሉ ተብሏል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ