ሕዳር 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርንና አሸባሪነትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል ሕጋዊ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን መጠቀም ወሳኝ መሆኑን አሳስቧል።
ባንኩ ዛሬ ሕዳር 3 ቀን 2018 ዓ.ም. ለአሐዱ በላከው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጡ የተፈቀደላቸውን የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ሥም ዝርዝር በይፋ አውጥቷል።

ከተዘረዘሩት የተፈቀደላቸው አስተላላፊዎች መካከል፤ ቀደም ሲል የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት እንዳይሰጥ ታግዶ የነበረውና ዋና መሥሪያ ቤቱ በአሜሪካ ቪርጂኒያ ግዛት የሚገኘው ራማዳ ፔይ (ካህ) ይገኝበታል።
ባንኩ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው፤ በድርጅቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ አጠቃላይ ግምገማ ከተካሄደ በኋላ እንደሆነ ገልጿል።
ይህ ውሳኔ በሀገሪቱ ሕግና ደንብ መሠረት በድርጅቱ ላይ አስፈላጊው የቁጥጥርና የክትትል ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ የተወሰደ እርምጃ መሆኑንም ጠቁሟል።
ብሔራዊ ባንክ፤ "ውጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎች ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ በሚያስተላልፉበት በማንኛውም ጊዜ ሕጋዊና ግልጽ የሆነ አካሄድ መከተላቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል" ብሏል።
ሕጋዊ ፈቃድ በተሰጣቸው የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በኩል ገንዘብ መላክ፣ ገንዘቡ ደኅንነቱ ተጠብቆና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርንና አሸባሪነትን በገንዘብ መደገፍን የሚፃረር አሠራር ተከትሎ ወደ ተቀባዩ እንዲደርስ እንደሚያደርግ አመላክቷል።
ባንኩ ሕዝቡ ፈቃድ የተሰጣቸውን የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ለይቶ ለማወቅ እንዲችል የሕጋዊ ድርጅቶችን ሥም ዝርዝር በድረ-ገጹ ላይ መመልከት እንደሚቻል አስታውቋል።
ብሔራዊ ባንክ፣ ዓላማው የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በግልጽነትና ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ብቻ እንዲሠሩ ድጋፍ ማድረግ መሆኑን አንስቷል።
አሁን አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደው የሚገኙ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በሙሉ የሀገሪቱ ሕግና ደንብ የሚጠይቀውን መስፈርት ለማሟላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ሲል ገልጿል።
ባንኩ ሕጋዊ የሐዋላ አገልግሎትን ለማበረታታትና የፋይናንስ ዘርፍን ጤናማ ዕድገት ለመደገፍ የሚረዳ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ግልጽና ቀልጣፋ የፋይናንስ ምኅዳር እንዲኖር ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ገልጿል።
ሕጋዊ ድርጅቶች መሆናቸው ከተገለጸላቸው 89 ተቋማት መካከል ቴሌብር ሬሚት፣ ሳፋሪ ኤም ፔሳ ሞባይል ፋይናንስ ሰርቪስ እና መኒ ግራም ይገኙበታል።
ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ፤ ባልተፈቀዱ የውጭ የሐዋላ ገንዘብ ማስተላለፍ ሥራዎች ላይ በተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ማስታወቁ አይዘነጋም።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ