ጥቅምት 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በማህበራዊ ሚዲያ ማንነታቸውን ደብቀው ሀሰተኛ መረጃዎችንና የጥላቻ መልእክቶችን በሚያሰራጩ አካላት ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን የቴክኖሎጂ ዲፕሎማሲን መፍጠር እንደሚያስፈልግ የኢንፎርሜሽ መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳንኤል ጉታ ገልጸዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን ያሉት ዛሬ በተካሄደው 6ኛው ብሄራዊ የሳይበር ደህንነት ወር ንቅናቄ ኮንፈረንስ ላይ በተደረገው የፓናል ውይይት ነው፡፡

"የሳይበር ደህንነት የዲጂታል ኢትዮጵያ መሠረት" በሚል መሪ ቃል ከጥቅምት 1 እስከ 302018 ዓ.ም በሚቆየው የሳይበር ደህንነት ንቅናቄ ወር አስመልክቶ በተዘጋጀው በዚሁ መርሃ ግብር ላይ፤ "ከስክሪን ባሻገር የማህበራዊ ሚዲያ ተፅእኖዎች" በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ተደርጓል፡፡
በዚህም የኢንፎርሜሽ መረብ ደህንነት አስተዳድር ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዳንኤል ጉቱ፤ በማህበራዊ ሚዲያ ማንነታቸውን ደብቀው ወንጀል የሚሰሩ አካላትን ለመቆጣጠርና ተጠያቂ ለማድረግ ፈታኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንን ችግር ለመፍታትም የቴክኖሎጂ ዲፕሎማሲን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ የሀገርን ብሄራዊ ጥቅሞች የሚጎዱ ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላትን ተጠያቂ ከማድረግ አንጻር የሕግ ክፍተቶች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ማንነታቸውን ደብቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለማወቅ አገልግሎቱን ከሚሰጡ ተቋማት ጋር የቴክኖሎጂ ዲፕሎማሲ መፍጠር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ከተቋማቱ ጋር ያለን ግንኙነት በማጠናከር ከሀገሪቱ ጥቅምና ፍላጎት አንፃር ጉዳት የሚያስከትሉ መረጃዎችን ማንነታቸውን ደብቀው የሚያሰራጩ አካላትን አሳልፈው እንዲሰጡ በማድረግ፤ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ የፕላትፎርም ወይም የአገልግሎቱ ሰጪ ተቋማት ጉዳት የሚያስከትሉ ይዘቶችን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ለይተው እንዳይሰራጩ መገደብ የሚችሉበት አሰራር ቢኖርም፤ አሰራሩ አካባቢያዊ አውዱን ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም ብለዋል፡፡
ከዚህ አንጻር ከባለቤቶች ጋር በትብብር መስራት ያስፈልጋል፤ እነሱም ከእኛ ጋር መተባባር እንዲችሉ የሚያደርጉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ከተቋማቱ ጋር በመደራደር መሠረተ ልማቶችን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገነቡ የሚያበረታቱ ፖሊሲዎችን ብናስቀምጥ መሠረተ ልማቶችን ሀገር ውስጥ በገነቡ ቁጥር የኛን ፍላጎትና ጥቅም ለማስከበር የመደራደር አቅማችንን ከፍ ማሳደግ እንችላለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ