ጥቅምት 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እንደከዚህ ቀደሙ በትምህርት ሚኒስቴር ምደባ ሳይሆን በተማሪዎቹ ምርጫ ይሆናል መባሉን ተከትሎ አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች ለህልውና አደጋ ተጋላጭ እንደሚሆኑ አሐዱ ያነጋገራቸው የትምህርት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

‎አሰራሩ ተማሪዎች በአካባቢያቸው የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችን ቀዳሚ ምርጫቸው ስለሚያደርጉ አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች ለህልውና አደጋ ተጋላጭ ያደርጋል ሲሉም ነው ባለሙያዎቹ የገለጹት፡፡

‎የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሒሳብ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሳሙኤል አሰፋ (ዶ/ር)፤ "ተማሪዎች በመረጡትና በፈለጉበት ዩኒቨርስቲ ሂደው እንዲማሩ መደረጉ ለተማሪዎች ጥቅም ቢኖረውም፤ በዩኒቨርስቲዎች የምናየው የተማሪዎች ስብጥርና 'ትንሿ ኢትዮጵያ' የሚለው እሳቤ ላይ ተፅእኖ ሊያሳድር ይችላል" ብለዋል። ‎

ዶክተር ሳሙኤል አሰፋ አክለውም፤ አሰራሩ በሁለት አይነት መንገድ ሊታይ ይችላል ያሉ ሲሆን፤ ጥቅምም ጉዳትም እንዳለው ገልጸዋል።

‎ተማሪዎች የሚፈልጉትን የትምህርት ዘርፍ ለመማር ዩኒቨርስቲው የሚሰጠውን የትምህርት አይነት አይተው ስለሚመርጡ ለተማሪዎች ጥቅም አለው፤ የሚታወቁ ዩኒቨርስቲዎች ብቻ በተማሪዎች ሲመረጡ አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች አለመሆናቸው እንደ ጉዳት ይወሰዳል በማለትም ገልጸዋል።

‎የትምህርት ባለሞያው አክለውም፤ "የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ሲታይ ተማሪዎች በራሳቸው ምርጫ ዩኒቨርስቲ ይገባሉ፣ በኢትዮጵያም ይተገበራል የተባለው የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እንደከዚህ ቀደሙ በትምህርት ሚኒስቴር ምደባ ሳይሆን በተማሪዎቹ ምርጫ ይሆናል መባሉ ጥሩ ቢሆንም አተገባበሩ ግን በአንድ ጊዜ ሳይሆን በሂደት መሆን አለበት" ብለዋል።

‎ሌላኛው የቀድሞው የጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት እና የትምህርት አማካሪ መንገሻ አድማሱ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ወደ መረጡት ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ መደረጉ ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር አናሳ መሆኑ እና ሀገሪቱ ካለችበት የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ አንፃር ሲታይ ለትምህርት ስርዓቱ ብቻ ሳይሆን ለተማሪዎቹና ወላጆች ጥቅም አለው ብለዋል።

‎ዩኒቨርስቲዎች ምን ያህል በተማሪዎች ይመረጣሉ? ወይም ይፈለጋሉ? የሚለውን ለመለየት የሚያሳይ ነው፤ በዚህም ዩኒቨርስቲዎች በተማሪዎች ለመመረጥና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል።

‎ትምህር ሚኒስቴር ይተገበራል ያለው አዲስ አሰራር ዩኒቨርስቲዎች የሚሰጡት የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል የሚያደርግ ቢሆንም፤ ነገር ግን ተመጣጣኝ ያልሆነ የተማሪዎች ቁጥር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድርግ ያስፈልጋል ሲሉ ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ