ጥቅምት 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የተያዘው የጥቅምት ወር ከቅዝቃዜ ወደ ሙቀት መሸጋገሪያ በመሆኑ ባለፉት ወራት ከነበረው ከፍ ያለ ሙቀት እና ንፋስ ስለሚኖር፤ በዚህ ምክንያት ከሚፈጠሩ አደጋዎች ማኅበረሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አሳስቧል፡፡
በኮሚሽኑ የአደጋ ቅነሳ ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ደሲሳ ጦና፤ "ያለፉት ዓመታት ተሞክሮ እንደሚያሳየው የጥቅምት ወር ከሌሎች ወራት በተለየ የእሳት አደጋ የሚስተዋልበት ነው" ብለዋል።
የአደጋውን መብዛት ምክንያቶች ሲያብራሩም፤ የወቅቱ ከፍተኛ ንፋስ የኤሌትሪክ መስመሮች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት፣ በቸልተኝነት የተተዉ ተቀጣጣይ ነገሮች የሚያስከትሉት አደጋ ዋነኞቹ መሆናቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች እና ተቋማት አደጋ ከመከሰቱ በፊት የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲወስዱ የጠየቁት ዳይሬክተሩ፤ ማኅብረተሰቡ ተቀጣጣይ ነገሮችን በሚጠቀምበት ወቅት ከከፍተኛ ጥንቃቄ ጋር እንዲሆንም አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በጥቅምት ወር በሚኖረው ከመደበኛው ከፍ ያለ ንፋስ ምክንያት አደጋ እንዳይከሰት የጥንቃቄ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ተጠየቀ
