በትላትናው ዕለት 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው ተካሂዷል፡፡
ምክር ቤቱ መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም በፕሬዝዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የቀረበውን የ2018 የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ የድጋፍ ሞሽንም አጽድቋል፡፡
በፕሬዝዳንቱ የቀረበውን ሞሽን መነሻ በማድረግ ከምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተውባቸዋል፡፡

ምክር ቤቱም የቀረበለትን የድጋፍ ሞሽን ውሳኔ ቁጥር 1/2018 አድርጎ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽም አጸድቋል፡፡
የሞሽን ውሳኔው ከመፅደቁ አስቀድሞ ግን የምክር ቤት አባላት በርከት ያሉ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል፡፡
በተለይም በሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ጥያቄዎች የተነሳላቸው ሲሆን፤ ጠቅላ ሚንስትሩ ምላሽና ማብራሪያም ሰጥተውበታል፡፡
የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና የማይፈልጉ ባዕዳን በጦርነት እንደማያሸንፉ ስለሚያውቁ በቅጥረኞችና ተላላኪዎች ምኞታቸውን ለማሳካት ቢጥሩም አይሳካላቸውም ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ለሚፈልጉ ኃይሎች መንግሥት በሩ ክፍት እንደሆነም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለምክር ቤቱ አሰረድተዋል፡፡
"ነገሮችን በሰላም ለመፍታት ትዕግስት ይጠይቃል" ያሉም ሲሆን፤ እንደመንግሥት የተከተሉትን ስትራቴጂም ያስረዳሉ፡፡
በዚህም 'ችግር አለብኝ' ከሚል ኃይል ጋር መዋያየት መፍትሄ መሆኑን ማመናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በዚህም 'ከሸኔ እና ከህወሓት ኃይሎች ጋር ተወያይተው ከፊሎቹ ወደ ሰላም መጥተው ስልጣን ላይ የሉም ወይ?" ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ማብራሪያ ላይ ከፊሎች ወደ ውይይት መምጣታቸውንና ስልጣን እንደተሰጣቸው በአፅዕኖት ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ እንደ 'ሀገር ለሚፈለገው ሰላም እና መረጋጋት በከፊል መወያየት እንዲሁም ስልጣን መስጠት በቂ ነው ወይ?'፤ 'የተሟላ ሰላም ለማምጣት ያልተቻለውስ ለምን ይሆን?' የሚሉ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡
ይህንን በሚመለከት የጠየቅናቸው የእናት ፓርቲው ዋና ፀሀፊ እና የአደረጃጃት ዘርፍ ኃላፊ አሰፋ አዳነ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

እንደእርሳቸው ሀሳብ በሀገሪቱ አሁን ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ባሉባቸው ቦታዎች ላይ ግጭቶች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
በእነዚህ አካባባቢዎች በስፋት እየተካሄደ ያለው ግጭት በሀገሩቱ ያለውን ፖለቲካዊ ቀውስ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሀሳባቸውንም ሲቀጥሉ 'ችግሩ የቱ ጋር ነው?' በሚል ሁሉን ያካተት ውይይት ማካሄድ ይገባ እንደነበር ያነሱ ሲሆን፤ የተወሰኑትን አስገብቶ ስልጣን መስጠት መፍትሄ አይሰጥም ብለዋል፡፡
በሁሉም ግጭት ባለባቸውና ግጭት የሚነሳባቸው የሚመስሉ አካባቢዎች ላይ ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ ውይይት መደረግ አለበት ብለዋል፡፡
በተለይም ደግሞ ከሸኔ እና ከህወኃት ጋር የተሳካ እና ያልተሳካ ውይይት መደረጉን ያስታወሱት ዶክተር አሰፋ፤ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋርም ውይይት ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ "ሕገ-መንግሥትና ሕግ ያለበት ሀገር ጋር ተለጥፎ ስለምርጫ መጠየቅ ተገቢ ነው ወይ?" ሲሉ ምክር ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ንግግራቸው ወቅት "ኢትዮጵያ ሲያምርባት አይኑ የሚቀላ፣ ሕዳሴ ሲያልቅ ከሰው ያጣላናል ለምን ያስፈልጋል?" የሚል አካል እንዳለ ተናግረዋል፡፡
"የባህር በር ጥያቄ ሲነሳ የሚሸማቀቅና የሚያፍር፣ ደፈር ብሎ 130 ሚሊዮን ሕዝብ ያስፈልገዋል ለማለት የሚተናነቀው፣ ለኢትዮጵያ ጥቅምና ብልፅግና ከጎኗ መቆም መድከም የማይሻ፣ ራሱን እንደ ማንጎ የሚቆጥር ግራዋ ነው" ሲሉ ስለታጣቂዎች ጠንካራ ትችታቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳብ በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት የእናት ፓርቲው አሰፋ አዳነ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ "ታጣቂዎችን 'ባዳ እና ዕዳ' ከማለት ይልቅ ወደ ስምምነት ማምጣቱ ለሀገር ይበጃል" ብለዋል፡፡
የሀገሪቱ ጠላቶች ተላላኪ እንዳያደርጓቸው ከተፈለገ ምህዳሩን በማስፋት ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ማሳደግ የሚበጀው መንገድ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
እውነተኛ እና ሀቀኛ ድርድር ማዘጋጀት እና ማመቻቸት የተሻለ መሆኑን የገለጹም ሲሆን፤ ሥም ከመሰጠት ማቅረብ የተሻለ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
ታጣቂዎች መግባታቸው መልካም መሆኑን የተናገሩት ደግሞ፤ ሙላት ገመቹ የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ናቸው፡፡

"አንድ አንዶች አመጣጣቸውም አወጣጣቸውም ጥያቄ የሚያስነሳ ነው" ያሉት ሊቀመንሩ፤ ወይ ተልዕኮ ተሳክቶ ወይ ደግሞ ሳይሳካለት የመጣ ይሆናል ብለዋል፡፡
ነገር ግን አሁንም ሰላም ባለመኖሩ ሁሉንም የሚያስማማ ውይይት መደረግ አለበት ሲሉም ሙላት ገመቹ ተናግረዋል፡፡
ሀሳባቸውን ሲቀጥሉም "በትላትናው ዕለት በነበረው ጉባኤ ላይ የተሰሙት አንድ አንድ ዛቻዎች ተገቢነት የላቸውም" ሲሉም ገልጸዋል፡፡
"እውነተኛ እርቅ ማምጣት ይገባናል" የሚሉት የኦፌኮው ምክትል ሊቀመንብር፤ አሁን እየተደረጉ ያሉ ለጥቂቶች የሚደረጉ የስልጣን እደላዋችን እንደመፋትሄ መውሰድ ሳይሆን ሁሉንም ያካተት ሰላም እንዲመጣ ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡
ታጣቂዎችም ጥያቄያቸው ስልጣን ከሆነ ስልጣን የሰፊው ሕዝበ በመሆኑ ምርጫ አድርጎ ስልጣኑን ሕዝብ እንዲሰጥ ማድረግ ይገባል ሲሉም አክለው ገልጸዋል፡፡
አቶ ሙላት ሲቀጥሉም፤ "በታጣቂዎችም በኩል ቢሆን ሲመቸው ጫካ ሳይመቸው ስልጣን ብሎ አቋም መኖር የለበትም" ብለዋል፡፡
በውጊያ ውስጥ ሲቆዩ ንብረት አውደመው ነብስ ማጥፋታቸው መረሳት የለበትም፤ ስለዚህ ተጠያቂነትም እንዳይሰፍን የሚያደርግ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትላትናው ምክር ቤት ውሎ በአማራ ክልል ታጣቂዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር ስለሚደረጉ ውጊያዎች ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ከሁለቱ ታጣቂ ቡድኖች ጋር ተወያይቶ የመጣውን ተቀብለናል" ይበሉ እንጂ፤ "ተላላኪ ናቸው ዓላማ የላቸውም" ሲሉ አጣጥለዋቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ 'ችግር አለብኝ' የሚል ኃይል ሁሉ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መጠየቅ እንዲችል መንግሥት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስተሩ፤ ከዚህ በፊት የታጠቁ ኃይሎች የሰላምን አማራጭ በመከተል ከመንግሥት ጋር ለሀገራቸው እድገት አብረው እየሰሩ መሆኑን ያስረዱ እንጂ ፓርዎቹ ግን "መንግሥት አሁንም የሚጠበቅበትን ከፍተኛ ሚና ሊወጣ ይገባል" ብለዋል፡፡