ጥቅምት 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎በሀገሪቱ የተፈጠሩና እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች አንዱ ምክንያት ብዝኃነትን ለመቀበል ዝግጁ አለመሆን እና ከብዝኃነት ጋር አብሮ ለመኖር የሚያስችል ስርዓት ማበጀት አለመቻሉ፤ ለፌዴራል ስርዐቱ ገቢራዊነት አሁንም ችግር ሆኖ መቀጠሉን የሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ለአሐዱ አስታውቋል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙሃንነት የለም ብሎ መቀበል አይቻልም፤ በሀገሪቱ አሁን ያለው ትልቁ ችግር ብዝሃነትን ለመቀበል ዝግጁ አለመሆን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

‎ሕብረ ብሔራዊ የፌደራል ስርዓትን ለመተግበር ብዙ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፤ በዚህም የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በሂደት ማሟላትና መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።

‎የአስተምህሮ ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አክለውም "ፌደራሊዝም ብሔርተኝነትን ማለዘብ አለበት" ያሉት ሲሆን፤ ፌደራሊዝምና ብሔርተኝነት አንድ ላይ የሚሄዱት ሁሉንም ብሔር አካታች የሆነ ሕብረ ብሔራዊ ስርዓት ሲኖር ብቻ ነው በማለት ገልጸዋል።

‎ሕብረ ብሔራዊ የፌደራል ስርዓትን ለመገንባት፣ ለማስቀጠል እንዲሁም ጫፍ የወጣ ብሔርተኝነትን ለማርገብ የሚቻለው፤ የሌሎችን ማንነት በመቀበል የአካታችነት ስርዓት ሲፈጠርና ሲረጋገጥ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

‎"ዋናው እና ትልቁ ጉዳይ ብዙሃንነትን ተቀብሎ ማስተዳደር ይሁን እንጂ ብሔርተኝነት የሚለውን አስተሳሰብ የምናብራራበት መንገድ በራሱ መስተካከል አለበት፤ ብሔርተኝነት ማለት ዘረኝነት ማለት አይደለም" ሲሉም ኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር) አብራርተዋል።

አክለውም፤ ብዝሃነትን ለማስተዳደር የፖለቲካ ጥያቄዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ጠንካራ የፌደራል ተቋማት ያስፈልጋል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

"እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ብዙ ብሔር ባለባት ሀገር ውስጥ በብዝሃነት ዙሪያ በስፋት ከመስራት አንፃር ክፍተት አለ" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ጥቂት የፌደራል ተቋማት ቢኖሩም በሚፈለገው ደረጃ እየሰሩ አለመሆኑን አንስተዋል።

‎"ብሔርተኝነት የውድድር ጉዳይ መሆን የለበትም፤ በመነጋገር ፤ በመወያየት እና በልዩነት ውስጥ በጋራ የመኖር አስተሳሰብ ሊሆን ይገባል፤ ለዚህም ጠንካራ የፌደራል ተቋማት ያስፈልጋል" ሲሉም ገልጸዋል።

‎"በሀገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ባህል ማስተካከል ካልተቻለ ብዝሃነትን ማስቀጠልና ማረጋገጥ አይቻልም፤ ብሽሽቅ ከበዛበት አካሄድ መውጣት ያስፈልጋል" በማለት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር) አሳስበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ