ጥቅምት 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ተከትሎ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ምርቶቿን ወደ ኬንያ፣ ሶማሊያና ደቡብ አፍሪካ መላኳ የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህም የራሱ የሆነ የንግድ ስትራቴጂ የተቀረጸለት መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኦኮኖሚ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለአፍሪካ ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የትግበራ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን የገለጹት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሃብረቢ ናቸው።

ስትራቴጂው በዋናነት ኢትዮጵያ የትኞቹ ምርቶች ላይ ነው ተጠቃሚ የምትሆነው፣ የትኞቹ ምርቶች ላይ ትኩረት መደረግ አለበት የሚለውና የሀገራቱ መዳረሻን በተመለከተ አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል።

ስትራቴጂው የሚገጥሙ ተግዳራቶችና የመፍትሔ ሃሳቦችን ጭምር የያዘ መሆኑ ጠቁመዋል።

ለዚህም የማስተግበሪያ ስትራቴጂው በአማርኛና በእግሊዝኛ እንዲታተም በማድረግ በማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ ተሰራጭቷል።

መንግሥት በዚህ ዘርፍ ላይ ነገሮችን የማመቻቸት ስራ ነው የሚሰራ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በግሉ ዘርፍ ላይ ያሉ ነጋዴዎች፣ ባለሃብቶች፣ ላኪዎች እና አምራቾች በስፋት ይሳተፋሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በ54 የአፍሪካ ህብረት ሀገራት ተፈርሞ እ.ኤ.አ ከግንቦት 30 ቀን 2019 ጀምሮ ጽ/ቤቱን በጋና አክራ ከፍቶ ወደ ትግበራ ሂደት የገባው የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ስምምነት፤ በአባላት ብዛት ትልቁ ነፃ የንግድ ቀጠና ነው፡፡

ስምምነቱ በመላ አፍሪካ አንድ ትልቅ የሸቀጦችና የአገልግሎቶች ገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ የኢኮኖሚ ነጻነትና እና ዕድገትን ለማምጣት፣ ድህነትን ለመቀነስ እና አህጉሪቱን በኢንዱስትሪ የማሳደግ አላማን በመያዝ ተመስርቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ