ጥቅምት 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሥራ ዘመኑ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እና የሚወጡ ሕጎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እንሰራለን ሲሉ አሐዱ ያነጋገራቸው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል፡፡
6ኛው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መስከረም 26 ቀን 2018 በይፋ መጀመሩ የሚታወስ ነው።
አሐዱም የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ጅማሮ ጋር በተገናኘ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን አነጋግሯል።
በዋናነት የወከላቸው ሕዝብ የሚያነሳቸውን የመሠረተ ልማት፣ የመዋቅር እና ሌሎች ጥያቄዎች በመንግሥት ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራቸውና ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሰሩ ለአሐዱ የተናገሩት፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የቁጫ ሕዝቦች ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራር ገነነ ገደቡ (ፕ/ር) ናቸው።

የምክር ቤት አባሉ አክለውም በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 55 ንዑስ አንቀፅ 1 መሠረት፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፌደራሉ መንግሥት ሕጎችን የማውጣት ስልጣንና ተግባር እንዳለው ገልጸዋል።
በንዑስ አንቀፅ 17 መሠረት ደግሞ ምክር ቤቱ ባወጣቸው አዋጆች መሠረት የሕግ አስፈጻሚውን አካል አሠራር የመመርመር ስልጣን እንዳለው ጠቁመው፤ በአዲሱ የስራ ዘመን የሚወጡና የወጡ ሕጎች በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆኑ የክትትልና ቁጥጥር ሥራን እንደሚሰሩ አብራርተዋል።
በዚህም ሕግ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል የሚወጡ ሕጎችን ማስፈፀሙን የመስክ ምልከታና የሪፖርት ግመገማን በማድረግ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ነው ያነሱት።
ሕግ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የሚወጡ ሕጎች ላይ ዜጎች ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ለተግባራዊነቱ አጋዥ እንዲሆኑ ይሰራል ሲሉ አሳስበዋል።
አሐዱ ያነጋገራቸው ሌላኛው የዘይሴ ምርጫ ክልል ሕዝብ ተወካይ እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ተመራጭ አቶ አብርሃም አሞሼ በበኩላቸው፤ "የወከላቸው ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ 'በአዲሱ የሥራ ዘመን' እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

በዋናነት መራጩ ሕዝብ የመዋቅርና፣ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኝ መመካከራቸውን ገለጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ሕግ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል በምክር ቤቱ የሚወጡ ሕጎችንና ፖሊሲዎችን በግልፅነትና ተጠያቂነት መርህ የመተግበርና የማስተግበር ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸው፤ ሕጎች በአግባቡ ተፈጻሚ በማይሆኑበት ወቅት በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ተጠያቂነትን ለማስፈን ክትትል እንደሚያደርጉ የምክር ቤት አባሉ ጠቁመዋል።
ለመረጣቸው ሕዝብ በመታመን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በአዲሱ የሥራ ዘመን እንሰራለን ሲሉም የምክር ቤት አባላቱ ለአሐዱ ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ