ሰኔ 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሁሉም ዕድሜ ክልል ለሚገኙ ተማሪዎች የልዩ ፍላጎት ትምህርት መርሃ ግብርን ጨምሮ የተለያዩ የትምህርት ዝርፎችን ተደራሽ የማድረግ አላማው ያነገበው፤ "አብነት የማህበረሰብ ት/ቤቶች" በዛሬው ዕለት የቦርዱ አባላት እና መሥራች አባላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ብሔራዊ ትያትር በይፋ ተመስርቷል፡፡
በዚህ የምስረታ መርሃ ግብር ላይም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ምሁራን፣ የአዲስ አበባ ከፍተኛ የትምህርት ዘርፍ መሪዎች፣ አንጋፋው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵዊያን፣ የተለያዩ የማህበረሰብ አባላት እና ጥሪ የተደረላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በግል ይተዳደር የነበረው አብነት አካዳሚ ተቋም "ትምህርት ቤቶች የሕብረተሰቡ ሀብት ናቸው" በሚል ተልዕኮ፤ ላለፉት 12 ዓመታት ትምህርትን በሁሉም አካባቢ ለሚገኙ ሕጻናት በጥራትና በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን የት/ቤቶቹ ቦርድ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዘላለም ተሾመ በመድረኩ ተናግረዋል።
ነገር ግን የባለቤትነት ድርሻ ሙሉ በመሉ የሕብረተሰቡ እንዲሆን ከየአካባቢው ሕብረተሰብ ጥያቄ ሲቀርብ በመቆየቱን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህን ተከትሎም ተቋሙ በዚህ መልክ ቢቋቋም ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚሰጠውን ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ሕጋዊ ሂደቶችን አልፎና አስፈላጊውን መስፈርቶች አሟልቶ "አብነት የማህበረሰብ ት/ቤቶች" በይፋ መመስረቱን አብራርተዋል።
ይህንንም ዓላማ ከግብ ለማድረስ ዘመናዊ እና ደረጃውን የጠበቀ ግዙፍ የትምህርት ማዕከል መመስረቱን የገለጹም ሲሆን፤ ማዕከሉ በአሁን ሰዓት አሳሳቢ የሆነውን የተማሪዎች የትምህርት ክፍያ ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ማህበረሰቡን ያማከለ ተመጣጣኝ ክፍያ ለማስከፈል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
በአብነት የማህበረሰብ ት/ቤቶች በመጪው በ2018 ዓ.ም ከዜሮ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ለማስተማር የታቀደ ሲሆን፤ 1 ሺሕ ተማሪዎችን ለመቀበል በዝግጅት ላይ ስለመሆኑም ተብራርቷል። በተጨማሪም ለ70 አስተማሪዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኢትዮጵያ ቀዳሚ የሆነው አብነት የማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች በይፋ ተመሰረተ
