መስከረም 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማነቃቃት የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ላይ ትኩረት በማድረግ፤ ለግል ኮንስትራክሽን ማኅበራት ቅድሚያ ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ለአሐዱ አስታውቋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ (ዶ/ር)፣ "መንግሥት የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ለሀገር ውስጥ ኮንስትራክሽን ማኅበራት ቅድሚያ ሰጥቷል" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
አንዳንድ የኮንስትራክሽን ተቋማት "መንግሥት ከሀገር ውስጥ ይልቅ ለውጭ ተቋራጮች ቅድሚያ እየሰጠ ነው" የሚል ቅሬታ እንዳላቸው ከአሐዱ ለተነሳላቸው ጥያቄ ዋና ዳይሬክተሩ ሲመልሱ፤ "መንግሥት የሚያሰራቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች የሀገር ውስጥ ተቋራጮች የመፈፀም አቅም በላይ ሲሆኑ ፕሮጀክቱ ለውጭ ኩባንያዎች ይሰጣል" ብለዋል።
አንዳንድ ሥራዎች ላይ የውጭ ኩባንያዎች መሳተፋቸው እና ቅድሚያ ማግኘታቸው አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ እንዳለም አብራርተዋል።
ፕሮጀክቶች ለውጭ ተቋራጮች ሲሰጡ የኩባንያዎቹ የመፈጸም አቅም እና የመምራት ችሎታ ታይቶ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተውበታል።
አክለውም "መንግሥት የሕግ ማዕቀፍ እያዘጋጀ ቢሆንም በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች አቅም ውስንነት አለ። ይህንን ድክመት ከውጭ ከሚመጡ ኩባንያዎች የአሰራር ሂደት፣ የቴክኖሎጂ እና የአፈጻጸም ብቃት በምንወስደው ልምድ አቅማችንን ለማሳደግ ልንጠቀምበት ይገባል” ብለዋል።
የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ ያለው ቢሆንም፤ ዘርፉ በሚገባው ልክ እንዳያድግ እንቅፋት ከሆኑ ነገሮች መካከል የግሉ ዘርፍ አለመጠናከር፣ የግዢ ሥርዓት ፍትሐዊ አለመሆን፣ ግጭቶችና የበጀት ማነስ፣ ለችግሮች አፋጣን እና ግልጽ የመፍትሄ አለመስጠት በዋነኝነት ተጠቅሰዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ባለስልጣኑ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማነቃቃት የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ አስታወቀ
